Fana: At a Speed of Life!

ጸሎተ ሐሙስ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን እራት የበላበት እና እግራቸውን በትሕትና ያጠበበት ዕለት ነው፡፡

በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዐቢይ ጾም በተለይ ደግሞ በዚህ በህመማት ሳምንት የተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች ይከወናል፡፡

እያንዳንዱ የሳምንቱ ቀናት የየራሳቸው ትርጉም ያላቸው ሲሆን ÷ እለተ ሐሙስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ በብዙ ስያሜ እንደሚጠራ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰባኪ ወንጌል ዲያቆን ምትኩ አበራ ይናገራሉ፡፡

ዲያቆን ምትኩ ከፋና ብሮድካስቲንግኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት÷የህመማት ሳምንት አራተኛ ቀን ጸሎተ ሐሙስ (ኢየሱስ ክርስቶስ ረጅሙን ጸሎት ያደረገበትና ቅዳሴም የቀደሰበት )፣ ህፅበተ ሐሙሥ ፣የምስጢር ቀን (የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ስጋ እና ደም እራሱ ፈትቶ የሰጠበት ሚስጢረ ቁርባን የተሰጠበት) እንዲሁም የሐዲሥ ኪዳን ሐሙሥ(ሀዲስ ኪዳን የተጀመረባት ሀሙስ) ይባላል፡፡

እንዲሁም የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ “የነጻነት ሐሙስ”ም ይባላል፤ እንደ እምነቱ አስተምህሮ በጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ በዓላዛር ቤት ከሃዋሪያት ጋር ማዕድ የቀረበበት ቀን ነው፡፡

ይህም ቀን ሚስጢረ ቁርባን የተገለጠበት ኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናን፣ ፍቅርን፣ መታዘዝን እንዲሁም ዝቅ ማለትን ያስተማረበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ይህን ቀን የምታስብ ሲሆነ ÷ በቀኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የጳጳሳቱን እግር ያጥባሉ፣ ጳጳሳቱም በተዋረድ የካህናቱን እግር በትህትና ያጥባሉ፤ካህናቱ ደግሞ የምዕመኑን እግር ያጥባሉ፡፡

በሌላ በኩል በዚህ እለት ጉልባን የሚበላ ሲሆን÷ ጉልባን፣ ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅ ምግብ ነው፡፡

ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸው የሚታሰብበት ከእስራኤላውያን የመጣ ሥርዓት ነው፡፡

ጉልባን እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን እና ለጊዜው የሚደርስ ምግብ እሱ በመሆኑ ያንን እንደሚበሉ ያስታውሰናል፤ይህን ታሪክ ለማሰብም በሰሞነ ሕማማት በተለይም በጸሎተ ሐሙስ ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል፡፡

በጸሎተ ሐሙስ የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፤ ይህም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ሁሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.