Fana: At a Speed of Life!

የጸሎተ ሐሙስ “ሕፅበተ እግር” ስነ ስርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ተከናወነ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢየሱስ ክርስቶስ የትህትና እና አክብሮት መገለጫ የሆነው የጸሎተ ሐሙስ ‘ሕፅበተ እግር” ስነ ስርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከናውኗል፡፡

ዕለቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የቤተክርስቲያኗ ጳጳሳት፣ ካህናት እና ምእመናን በተገኙበት በመንበረ-ፓትሪያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ቤተክርስቲያን ተካሂዷል።

የሃይማኖቱ ተከታዮችም ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትሕትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትን የጸሎተ ሐሙስ ዕለት በቅዳሴ፣ በስግደት እና በሕፅበተ እግር አክብረዋል።

በቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ ካህናት አባቶች በዕለተ ሐሙስ በዕውቀት፣ በዕድሜ፣ በክብር፣ በስልጣን ትልቅ ነኝ ሳይሉ ከዲያቆናት እስከ ምዕመናን ድረስ ዝቅ ብለው እግር በማጠብ የክርስቶስን ትህትና በተግባር ይሰብካሉ።

በዛሬው ዕለትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የጳጳሳቱን እግር በማጠብ የኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናና አክብሮት መገለጫ የሆነውን የ“ሕጽበት እግር” ስነ ስርዓት አከናውነዋል።

በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ገዳም የስብከተ ወንጌል ፀሐፊ ዲያቆን ነብዩ ኤልያስ እንደገለጹት÷ የዛሬዋ ዕለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ስፍራ የሚሰጣት ናት።

ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ዕለት የሐዋርያቱን እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ በማጠብ ፍቅርን እና ትህትናን ማስተማሩን እና የኦሪት መስዋዕትን በመሻር የሐዲስ መስዋዕትን መስራቱንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ማህበረሰቡ የዕለቱን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ በተግባር በመላበስ እንግዳ ተቀባይነትን፣ ፍቅርን፣ ሰዎችን ማክበርን እና ትህትናን የዘወትር ተግባሩ ሊያደርግ እንደሚገባ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.