Fana: At a Speed of Life!

አቶ ጥላሁን ከበደ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጲያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቼ፤ እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!

ትንሣኤ በክርስትና እምነት ጥልቅ ትርጉም ያለው፤ ክርስቶስ የአዳምን ዘር ከበደል ቀንበር ነፃ ያወጣበት፤ ለሰው ልጆች ምሕረትና ድኅነት፤ ሰላምና ፍቅር የተገኘበት በድምቀት የሚከበር ታላቅ በዓል ነው፡፡

በዓለ ትንሣኤው የዕርቅ፤ የይቅርታና የሰላም መገለጫ ነው፡፡ በሰውና በፈጣሪ መካከል የነበረ የጥል ግድግዳ በአምላክ ይቅር ባይነት የፈረሰበት፣ ዕርቅና ሰላም ወርዶ አዲስ የምሕረት ምዕራፍ የተከፈተበት በመሆኑ በዓሉን ስናከበር ቂም፤ ቁርሾና በቀልን በይቅርታ በመሻገር ሊሆን ይገባል፡፡

ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው፡፡ ሰላም በለሌበት የምናቅደውና የምንፈጽመው ልማት፤ የምናልመው ለውጥ እና የተሻለ ነገ አይኖርም፡፡ ሰላም ፍሬዋ ዕድገት፤ ልማትና ሁለንተናዊ የጋራ ብልጽግና ነው፡፡

ሰላም ክርስቶስ በትንሣኤው ያደለን፤ በዋጋ የማይተመን ከነገሮች ሁሉ የበለጠ መሆኑን ተረድተን ለጋራ ሰላማችን በጋራ መቆምን የበለጠ የምናጠናክርበት አጋጣሚ መሆን ይኖርበታል።

ትንሣኤ የጽናት፤ የተስፋ እና የድል በዓል ነው፡፡ ለሰው ልጆች ሁሉ የተስፋ ምልክት፤ ጨለማና ሞት የተሸነፉበት የፅናትና የድል ተምሳሌት ነው፡፡

በዓሉን ስናከብር በየወቅቱ የሚገጥሙንን ጊዜያዊ እና ተለዋዋጭ ፈተናዎች በፅናት በማለፍ ለቀጣይ ድል መብቃት እንደምንችል በማሰብ ሊሆን ይገባል።

የክርስቶስ ትንሣኤ የፍቅርና የእውነት ኃያልነት የተገለጠበት በመሆኑ በዓሉን የእምነቱ አስተምህሮ በሚያዘው መሠረት ፍቅርን በመስበክና አብሮነትን በማጠናከር እናክብር።

በተለይ ቅጥፈት ምን ብትበረታ የማታ ማታ በእውነት መረታቷ ተጨባጭ መሆኑን ከትንሣኤው በመማር በከፋፋይ ነጠላ ትርክቶች ሳንሸበር፤ ለሀሰት ዘመቻዎች ጆሮ ሳንሰጥ አንድነታችንን በጽኑ የሕብረ-ብሔራዊ መሰረት ላይ አጽንተን ልማትና ብልጽግናችንን እውን ማድረግ እንደሚገባን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በዓለ ትንሣኤው የፍጹም ትህትናና የመታዘዝ ተምሳሌት ነው፡፡ በዓሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ትህትናን በመማር በተሰማራንበት መስክ ህዝብን በፍጹም ቅንነትና ታማኝነት ዝቅ ብሎ በማገልገል የክርስቶስን ትህትና በተግባር ለመኖር ራስን የምናዘጋጅበት ነዉ፡፡

በአጠቃላይ በዓሉን ስናከብር ያጡትን በማሰብ፤ የተቸገሩትን በመርዳት እና መልካም ሥራን በመስራት መሆን ይኖርበታል፡፡

ከእምነቱ አስተምህሮ እንደምንረዳው ክርስትና ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ ፍሬ የምናፈራበት የዕድገት ጉዞ እንጂ በምንሠራት ጥቂት በጎ ተግባር የምንወሰንበት አይደለም፡፡

በመሆኑም መረዳዳቱና መደጋገፉ በዕለተ ፋሲካው ሳይገደብ በየአካባቢው የተቸገሩ ወገኖቻችንን በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲችሉ ለማቋቋም በመተባበር ሊቀጥል ይገባል፡፡

በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ።

በድጋሚ መልካም የትንሣኤ በዓል!!
ፈጣሪ ሀገራችንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.