Fana: At a Speed of Life!

የትንሳኤ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታና ምህረትን የሰጠበት፤የጥልና የመለያየት ግድግዳን አፍርሶ የሰውን ልጅ የታደገበት ነው – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) (ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) (ኢ/ር) ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷የትንሳኤ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን ፅኑ ፍቅር በመስቀል ላይ ያሳየበት እንዲሁም ይቅርታና ምህረትን ለሰው ልጆች የሰጠበት፤ የጥልና የመለያየት ግድግዳን አፍርሶ የሰውን ልጅ የታደገበት መሆኑን አውስተዋል፡፡

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩት መንፈሳዊ በዓላት አንዱ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ይህ የትንሳዔ በዓል መታዘዝን፣ይቅርታንና ምህረትን እንዲሁም አንዱ ለሌላው መተሳሰብ እንዳለበት የሚያስተምር መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር መረዳዳትንና መጠያየቅን ከተለመደው ባህል ባለፈ በፍጹም መንፈሳዊነት ስሜት በጎዳና ላይ የወደቁትን በማሰብ፣ በህግ ጥላ ስር ያሉትን በመጠየቅ፣ታመው የተኙትን በማጽናናትና ካለን ላይ በማካፈልና በአብሮነት መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በደል ተላልፎ በመሰጠት የሰውን ልጆች ከጨለማ ወደ ብርሃን ነጻ ለማውጣት ዋጋ የከፈለበት በመሆኑ እኛም አቅመ ደካሞችን በመርዳትና ካለን በማካፈል፣ለወገኖቻችን በመድረስና በመተሳሰብ በዓሉን ማከበር አለብን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የትንሳኤ በዓል ለክልሉ ህዝቦች እንዲሁን ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሰላም፣ የበረከት፣ የመተሳሰብና የፍቅር እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.