Fana: At a Speed of Life!

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች የከፈለው መስዋዕትነት ለዓለም ዕርቅና ይቅርታ በር የከፈተ ነው – አቶ ፍቃዱ ተሰማ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች የከፈለውመስዋዕትነት ለዓለም ዕርቅና ይቅርታ በር የከፈተ ነው ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ገለጹ፡፡

አቶ ፍቃዱ ተሰማ ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ውድ የክልላችን እና የሀገራችን፣ እንዲሁም በመላው ዓለም የምትገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ፤ እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው በሠላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ።

የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የዛሬንና የወደፊት የሕይወት ተስፋን የሰነቀና ከዘመን-ዘመን ተሻጋሪ የሆነ፣ በብዙ ጥልቅ የህይወት ሚስጢር እያጌጠ የሚከበር ታላቅ መንፈሳዊ በዓል ነው።

ቅዱሳት መጻሕፍትና የሐይማኖት አባቶችም፥ በክርስትና እምነት አስተምህሯቸው፥ የስቅለትና የትንሣዔ በዓል ትርጉም፣ እጅግ የረቀቀና ጥልቅ ሚስጢር የተገለጠበትና የመለኮታዊ ጉዞ ዕቅድም ቁልፍ መዳረሻ ነው በማለት ያስገነዝባሉ።

የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ለሠው ልጆች ሁሉ እርቅን፣ ምህረትንና ይቅርታን በማወጅ በዓለም ዙሪያ ሠላምን ከማስፈኑም ባሻገር ጥላቻን በፍቅር ተክቶ በሠውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጠቡን ግድግዳ በደሙ ያፈረሰና ኩነኔን በማስወገድ ርቀው ለነበሩት የሠላምን ወንጌል የምስራች ብሎ የሰበከ፤ የተራራቁትን በማቀራረብና የተጣሉትንም በማስተራረቅ የጽድቅን መንገድ የከፈተ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ያሰፈነም ጭምር እንደሆነ በቅዱስ ቃሉ ተፅፎ ይገኛል፤

ውድ የክልላችን እና የሀገራችን እንዲሁም በመላው ዓለም የምትገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ፤

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ኃጢአት የከፈለው መስዋዕትነት የጥላቻና የክፋትን ምዕራፍ ዘግቶ፤ የፍቅር፣ የእርቅና የሠላም መርሆዎችን፣ እንዲሁም የዘላለምን ሕይወት መንገድን በማብሰር ይቅርታ የአሸናፊዎች መንገድ መሆኑን ነፍሱን በመስቀል ላይ በመስጠት ፍቅር በተጨባጭ አረጋግጧል።

እኛም ዛሬ የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ ስናከብር ሁል ጊዜ የእለት ተእለት የህይወታችን መርሆ ማድረግ ያሉብን በርካታ ቁም ነገሮች እንዳሉ ልንገነዘብ ይገባል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የድህነትንና ኋላቀርነትን ታሪክ በመቀየር ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ብሩህ ተስፋ ላይ ትገኛለች። በየዘመናቱ ያጋጠሟትን ችግሮችና ፈተናዎችን ወደ ዕድል ቀይራ በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበች የምትገኘዋ አገራችን ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤታችን በመሆኗ ዛሬም እንደ ትላንቱ ከፍ ባለ አገራዊ አመለካከትና ስሜት ልንጠብቃት፣ ልንንከባከባትና ልንገነባት ይገባል።

ዛሬ ከብረት የጠነከረ አንድነታችንንና ህልውናችንን የሚፈታተኑ ፈተናዎችን ለመከላከል ለጋራ ዓላማ በመቆም፣ ለእውነተኛ ወንድማማችነትና እኩልነት ወደፊት መገስገስ ይኖርብናል። አብሮ የመኖር ባህላችንም እንዲዳብር ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር ብቻ እንዲፈቱ ለማድረግ ተግቶ መስራት ያስፈልጋል።

የሰላም፣ የእርቅ፣ የምህረት እና የይቅርታ መንገዶች ወደ ስኬት ያሸጋግራሉ። ካሰብነው ግብ ለመድረስ እና ራዕያችንን እውን ለማድረግ በዚህ አቅጣጫ ብቻ እንድንጓዝ ይገድበናል። በመሆኑም በአገራችንና በክልላችን በሚገኙ የተለያዩ አከባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፍትሔ እንዲያገኙ እና አንድነታችንን የሚፈታተኑ ማነቆዎች በዕርቅና በይቅርታ እንዲፈቱ መተባበር ይጠበቅብናል።

የብልፅግና ራዕይ ከግብ ሊደርስ የሚችለው በሁሉም ዜጎች የነቃ ተሳትፎ በመሆኑ ዜጎች በተለያዩ የልማት መስኮች፣ የፀጥታ ሥራና በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱና ከብልፅግና ጉዞአችን ሊያደናቅፉን፣ ወደ ኋላ ሊያስቀሩን፣ አንድነታችንን የሚፈታተኑ ኋይሎች ፊት በጋራ መቆም ይጠበቅብናል።

በትንሣዔው በዓል የተጎናፀፍናቸውን መንፈሳዊ ነፃነት ጠብቀንና አጠናክረን በማስቀጠል በቃሉ መሠረት ያለው ለሌለው በማካፈል፣ እርስ በርሳችን በመተሳሰብና አንዱ ከሌላው ጎን በመቆም በከፍተኛ የወንድማማችነት መንፈስ በዓሉን ማክበር እንደሚገባን ጥሪዬን እያስተላለፍኩ በዓሉ ለሁላችንም የሠላም፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆንልን እመኛለሁ።

መልካም በዓል
አቶ ፍቃዱ ተሠማ
በብልፅግና ፓርት የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.