Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ”በኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የ312 ባለሀብቶችን ችግር መፍታት ተቻለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ”በኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወነ ሥራ የ312 የባለሀብት ኢንዱስትሪዎች ችግር ተፈትቶ ወደ ምርት መግባታቸውን የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡

በዚህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካትና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸው÷ ወደ ምርት የገቡት ኢንዱስትሪዎች ከ82 ሺህ 300 ለሚልቁ ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል፡፡

ክልሉ በግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕምቅ ፀጋ እንዳለው ጠቅሰው÷ ፀጋዎችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማፋጠንና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ፀጋዎችን በመለየት፣ የምርት አይነቶችን በመወሰንና አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ በማስገባት በክልሉ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ተቀርጾ እየተተገበረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ዓመትም በ28 የኢንዱስትሪ መንደሮች ከ3 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት በመለየትና መሰረተ ልማት በማሟላት የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄን ለማጠናከር የሚያስል ሥራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በድሬዳዋ አሥተዳደር በንቅናቄው ለዘርፉ በተደረገ ድጋፍ እና ክትትል ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ከንቲባ ከድር ጁሃር ገልጸዋል፡፡

ለአምራቹ ዘርፍ የመሬት አቅርቦት ማመቻቸትና ከፋይናንስ እና ከሕግ አኳያ የነበሩ ክፍተቶችን መፍታት መቻሉን ገልጸው÷ ማበረታቻዎችን በመጠቀምም ተዘግተው የቆዩ ሰባት ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት መመለሳቸውን ለኢዜአ አስረድተዋል፡፡

ወደ ምርት የገቡ ኢንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ መሆናቸው ጠቁመው÷ ባለፉት ስድስት ዓመታት ወደ አገልግሎት የተሸጋገሩ ኢንዱስትሪዎች ከ16 ሺህ በላይ የሥራ ዕድልመፍጠራቸውን ተናግረዋል።

እነዚህን ውጤቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና በኢትዮጵያ ታምርት የተገኙ ውጤቶችን ለማሳደግ በቀጣይ የተሻለ ሥራ እንደሚከናወንም አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.