Fana: At a Speed of Life!

የአካባቢ ብክለትን በቸልታ ማለፍ ለትውልድ ከባድ እዳ መተው እንደሆነ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሁን ላይ የአካባቢ ብክለትን በቸልታ ማለፍ ለትውልድ ከባድ እዳ መተው ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ ተናገሩ።
 
የዓለም የጤና ድርጅት ለአካባቢ ብክለት መጠን ካስቀመጠው ልኬት አንፃር የአዲስ አበባ ከፍተኛ አብላጫ ያለው በመሆኑ የከተማዋ የአየር ብክለት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመላክት እንደሆነ ተነግሯል።
 
ይህንን አሳሳቢ የአካባቢ ብክለት በመከላከል ንጹህና ጽዱ ሀገርን ለትውልድ ለማስረከብ “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሀሳብ በመጋቢት ወር ንቅናቄ ተጀምሯል።
 
አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ፣ ፅዱ፣ ማራኪና ከአካባቢ ብክለት የፀዳች ለማድረግ በቀጣይ 6 ወራት የሚተገበር በአካባቢ ብክለት መከላከል ላይ ያተኮረ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ ሚያዚያ 11 ተጀምሮ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡
በንቅናቄ መርሃግብሩ ከተያዙ እቅዶች አንዱ በፕላስቲክ ብክለት ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር ሲሆን፤ ታዋቂና ተፅእኖ ፈጣሪ ከሆኑ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የኮሙንኬሽን ባለሙያዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።
 
በውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ የአካባቢ ብክለት የዓለም አሳሳቢ ነገር ነው ብለዋል።
 
አሁን ላይ የአካባቢ ብክለትን በቸልታ ካለፍን ለትውልድ ከባድ እዳን ነው የምንተወው በማለት ገልጸው፤ ይህንን ስጋት ለመቅረፍም ንቅናቄው መጀመሩን አንስተዋል።
 
የንቅናቄውን ዓላማ እውን ለማድረግ ተፅዕኖ ፈጣሪና ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሆኑ አካላት ግንዛቤ እንዲኖራቸው አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።
 
በሃይማኖት ኢያሱ እና ቃለአብ ግርማ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.