Fana: At a Speed of Life!

ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው 480 ተጠቋሚዎች መመዝገቡን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው ባካሄደው 2ኛ መደበኛ ስብሰባ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዕጩ ምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂና ዕንባ ጠባቂዎች ምዝገባ አፈፃፀም ሪፖርትና ዝርዝር የምልመላ መስፈርቶች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በሂደቱም አድናቆት የሚሰጠው ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ መመዝገቡን ኮሚቴው የገለጸ ሲሆን÷ በሪፖርቱም ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው 480 ተጠቋሚ ዕጩዎችን መመዝገቡን አስታውቋል፡፡
የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃ የአፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦለት ተወያይቷል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ÷ በምዝገባ ሂደቱ በመላ ሀገሪቱ ሕዝቡ ያደረገውን ተሳትፎና ባለሙያዎቹ በእረፍት ቀናቸው ሳይቀር ለመመዝገብ ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል፡፡
ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው በሚያስቀምጠው አቅጣጫና በምልመላ መሥፈርቱ መሠረት በፍጥነት እንዲከናወን ጠቁመዋል፡፡
ለምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ 200፣ ለዘርፍ ዕንባ ጠባቂ 85 እና ለሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ዕንባ ጠባቂ 195 በድምሩ 480 ተጠቋሚዎች መቅረባቸውን የኮሚቴው ፀሐፊ አቶ ዕውነቱ አለነ ገልጸዋል።
የምዝገባ ሂደቱ ተጠቋሚ እጩዎችን ለመቀበል በስልክ፣ በኦን ላይን እንዲሁም በጥቆማ ለሚያቀርቡ ጠቋሚዎች የመጠቆሚያ ሳጥኖች በማዘጋጀትና በሚዲያ ሽፋን መሠጠቱን አቶ ዕውነቱ አለነ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት አብራርተዋል።
ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው በጥልቀት ተወያይቶ ውድድሩን በውጤታማነት ለማጠቃለል የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማሳለፉንም የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
በዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው ተጠቋሚዎችን በመለየትና በጥንቃቄ በማወዳደር የተሻለ ውጤት ያመጡትን ዕጩዎች ለሕዝብ በይፋ እንደሚገልፅ ተመላክቷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.