Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በለውጡ ዓመታት ሕዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎች ዕውን ሆነዋል አሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት ፈተናዎችን በመቋቋም ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ሥራዎች ዕውን መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡

በወለጋ ሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ የተካሄደ ሲሆን÷ በሰልፉ ከአራቱም የወለጋ ዞኖች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

አቶ ሽመልስ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ የልማት ድሎች መመዝገባቸውን ጠቅሰው÷ ለአብነትም በስንዴ ልማት፣ አረንጓዴ ዐሻራ፣ መሠረተ-ልማት ተደራሽነትና በሌሎች የልማት ሥራዎች ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ልማትን ለማስቀጠል የተጀመሩ ሥራዎች በሁሉም መስክ ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የልማት ኢንሼቲቮች በክልሉ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ እያደረጉ ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመሆን የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበው፤ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት፣ ልማትን ለማደናቀፍ እና ሰላም እንዳይረጋገጠ ለማድረግ የሚሠሩ አካላትን ሕዝቡ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሊታገላቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ወለጋ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ የሚኖሩበት አካባቢ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህን አብሮነት በማጠናከር ሁሉም ለሰላም መስፈንና ልማት መረጋገጥ በጋራ እንዲሰራም ጠይቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.