Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መርሐ ግብር ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መርሐ ግብር እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ጀሉ ዑመር (ዶ/ር)÷ ዩኒቨርሲቲውን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ሙሉ ራስ ገዝ ለማስገባት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በቅደመ ምረቃና ድህረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች ተመርቀው ኢንዱስትሪ ውስጥ ለሚገቡ ተመራቂዎች ራሱን የቻለ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መርኃ ግብር መስጠት ለመጀመር መወሰኑን ነው ያነሱት።

ፕሮግራሙ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና የገበያውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሲሆን÷ መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጥ እንደሆነም አስታውቀዋል።

የፕሮግራሙ መጀመር በሥራ ገበያው ውስጥ ብቁ ሙያተኞችን ለማግኘትና የዩኒቨርሲቲውን አቅምና ብቃት ያለው ባለሙያ የማፍራት ተልዕኮ የሚያሳካ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሙያ ብቃት ማረጋገጫው በሁሉም ዘርፎች ላይ እንደሚሰጥ ጠቁመው÷ ይህ የሚመራበት አሰራር ይዘረጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በትምህርት ስርዓት ውስጥ ያሉ ተማሪዎችም ሆኑ በስራ ገበያ ያሉ ሰራተኞችና ምሁራን ለተማሩበት ሙያ የብቃት ማረጋገጫ ወይም ፕሮፌሽናል ሰርትፊኬት መውሰድ እንደሚችሉ ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.