Fana: At a Speed of Life!

ፈጣን የነዳጅ አቅርቦት ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሠራ መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የነዳጅ ዲፖ ግንባታንና የማጓጓዣ አማራጭን በማስፋት ፈጣን የነዳጅ አቅርቦት ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ገለጸ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ÷ በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም የተጀመረው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ የመንግሥትን የዕዳ ጫና በመቀነስ፣ የኅብረተሰብን ተጠቃሚነትና የነዳጅ ኮንትሮባንድን በመቀነስ ወሳኝ ሚና መጫወቱን ገልፀዋል።

በዚህም 190 ቢሊየን ብር የነበረውን የመንግሥት የዕዳ ክምችት ወደ 100 ቢሊየን ብር ማውረድ መቻሉን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

በሁለት ዓመት ውስጥ የሕዝብ አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች 29 ቢሊየን ብር ድጎማ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የነዳጅ ድጎማን ቀስ በቀስ ለማስቀረት ባስቀመጠው አቅጣጫ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አሠራርን የጣሱ ተሽከርካሪዎች ከስምሪት እንዲወጡ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡

የነዳጅ ዋጋን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን መደረጉ ኮንትሮባንድን በእጥፍ በመቀነስ እመርታዊ ለውጥ ማምጣት እንደቻለም ነው ያስረዱት፡፡

የፖሊሲ ማሻሻያው ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ 1ሺህ 500 የሚሆኑት የነዳጅ ማደያዎች የሥርጭት አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል፡፡

የማጓጓዣና ተያያዥ ወጪዎችን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም የነዳጅ ገበያ ዋጋ የነዳጅ ሽያጭ አገልግሎት እየሰጠች መሆኗንም ጠቅሰዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የነዳጅ ማደያ ደረጃ ተዘጋጅቶ እየተሰራበት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ 60 በመቶ የነበረውን የነዳጅ ስርጭት ወደ 45 በመቶ በክልሎች ደግሞ ከ40 በመቶ ወደ 55 በመቶ በማመጣጠን ፍትሐዊ የነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭት መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።

የዲጂታል ነዳጅ አስተዳደር ከወደብ እስከ ማደያ ያለውን የስርጭት ሂደት በቀላሉ ቁጥጥር የሚደረግበትን ትልቅ አቅም እንደፈጠረም አንስተዋል።

98 ከመቶ በሚሆኑት ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ላይ ዘመናዊ አሠራር በመዘርጋት የነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭት ሥራን በቀላሉ መቆጣጠር እየተቻለ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የተቀመጠውን የነዳጅ ሥርጭት አሠራር በመተላለፍ ያልተገባ አካሄድ በሚከተሉ ማደያዎች ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

በቀጣይም የገንዘብና የእሥራት ቅጣትን ጨምሮ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል አዋጅ ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትም አስተማማኝ የነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭት እንዲኖር ለማስቻል አዋሽ፣ ጅቡቲና ድሬዳዋ ላይ ትልልቅ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዲፖ እየገነባ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ከተሽከርካሪ በተጨማሪ በባቡር ትራንስፖርት በማጓጓዝ የነዳጅ አቅርቦትና ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ያነሱት፡፡

የነዳጅ ማጓጓዝ ስራ በሚካሄድባቸውና የጸጥታ ችግር አለባቸው በሚባሉ አካባቢዎች ጭምር ያለአንዳች መስተጓጎል ሥርጭት እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመደበኛ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ላይ ችግር እንደሌለ ጠቁመው፤ አልፎ አልፎ የሚከሰተው መስተጓጎልም የልማት ፕሮጀክቶች ከሚጠቀሙት የነዳጅ ፍላጎት የሚመነጭ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በጸጥታ ችግር ምክንያት የተስተጓጎለ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪም ሆነ ማደያ እንደሌለ ጠቁመው፤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች የነዳጅ ስርጭት ስራ በልዩ ትኩረት መከናወኑን አስታውቀዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ከፍተኛ የነዳጅ ፍላጎት መኖሩን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

ከመደበኛው የነዳጅ ስርጭት በተጨማሪም ለሚከናወኑ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች የሚውል የነዳጅ አቅርቦት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.