Fana: At a Speed of Life!

የጃፓኑ የሕትመት ፋብሪካ በኢትዮጵያ የማምረት ሥራ ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጃፓኑ የሕትመት ፋብሪካ ቶፓን ግራቪት በኢትዮጵያ የማምረት ሥራ ሊጀምር መሆኑ ተገለጸ፡፡

ኩባንያው በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሚገነባው ፋብሪካ ከፍተኛ ጥራት እና ሚስጢራዊ የመለያ ዘዴ የሚኖራቸውን ሕትመቶች እንደሚያመርት ተገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ÷የኩባንያው በኢትዮጵያ ሥራ መጀመር ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል የምታደርገውን ጉዞ የሚያፋጥን ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የደህንነት መስፈርቶችን የሚያሟሉ ሚስጢራዊ ሕትመቶችን ለማተም እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበርም ምርቶቹን ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት እንደሚያስችል ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው÷በኢትዮጵያ ያሉ የጃፓን ኩባንያዎች ውጤታማ መሆን ሌሎች የጃፓን ኩባንያዎችን እየሳበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የቶፓን ኔክስት ዋና ስራ አስፈጻሚ ቺ ቶንግ ዮ÷ዓላማችን ኢትዮጵያን የአፍሪካ የምርት ማዕከል ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ የመማሪያ መጽሐፍትን በማተም በትምህርት ዘርፉ ላይ እያገጣመ ያለውን የመጽሐፍ እጥረት ለመቅረፍ ይሰራልም ተብሏል።

የፓስፖርት ህትመትን በኩባንያው ለማሳተም ከስምምነት ላይ መደረሱ ን እና የኢ-ፓስፖርት አገልግሎትን ለማስጀመር በጋራ እንደሚሰሩ በኢትዮጵያ የቶፓን ግራቪቲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቃልኪዳን አረጋ ተናግረዋል።

ስምምነቱ ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የፓስፖርት እጥረት ለመቅረፍና ደንበኞችን በአገልግሎቱ እርካታ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ናቸው፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ÷የቶፓን ግራቪት ሥራ መጀመር ተኪ ምርቶችን በማምረትና የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት የልማት ኮርፖሬሽኑን ግብ ለማሳካት ያግዛል ብለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃያት ካሚል፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ እና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.