Fana: At a Speed of Life!

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች ለሀገር ውስጥ ገበያ ምርት እንዲያቀርቡ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች 50 በመቶ ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ መፈቀዱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)÷ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታትና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ የአምራች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች ምርታቸውን ሙሉ በሙሉ ለውጭ ገበያ እንጂ ለሀገር ውስጥ ማቅረብ ሳይፈቀድላቸው መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባለሃብቶችን ለማበረታታት በፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች 50 በመቶ ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ በአዋጅ መፈቀዱን ገልፀዋል።

እርምጃው ኩባንያዎች ምርታት ከማሳደግ ባለፈ የገበያ ዋጋ በማረጋጋት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

በቅርቡ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አዋጅ መውጣቱን ጠቀሰው÷ አዋጁ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ ዞን እንዲሸጋገሩ የሚያደርግና በማክሮ ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡

ከከተሞች መስፋፋት እና በሊዝ መሬት አቅርቦት ዙሪያም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን መፍታት የሚችል የፖሊሲ እርምጃ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል የውጭ ኩባንያዎች ዝግ በነበሩ ዘርፎች በችርቻሮም ሆነ በጅምላ ንግድ እንዲሳተፉ የሚፈቅደው መመሪያ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ትልቅ ዕድል ነው ማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የገቢና ወጪ ንግዱ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መደረጉ በአነስተኛ ባለሃብቶች ተይዞ እና ብዙኃኑ በሚማረርበት የአቅርቦት ገበያና የተጋነነ ዋጋን በማቃለል ረገድ ወሳኝ እርምጃ እንደሆነም አንስተዋል።

ለገበያው በሕግ የሚመራ ሥርዓት መበጀቱ ተወዳዳሪነትን፣ የምርት ጥራትን የሚጨምር እና ሸማቹን የሚደግፍ እንደሆነም ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.