Fana: At a Speed of Life!

አቶ ፍቃዱ ተሠማ የወለጋ ህዝብ ለሀገራዊ ለውጡ ላሳያው ድጋፍ አመሰገኑ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሠማ የወለጋ ህዝብ ለሀገራዊ ለውጡ ላሳያው ድጋፍ ምስጋና አቀረቡ፡፡

አቶ ፍቃዱ ጉዳዩን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ በርካታ ስመ ጥር ምሁራንና ጀግኖችን በማበርከት ሀገር ሲገነባ ለኖረው የወለጋ ህዝብ ሰላም፣ ልማት እና ብልፅግና እንጂ ስቆቃ እና እንግልት አይገባው ብለዋል፡፡

ሆኖም ግን ላለፉት አምስት አመታት ልማት፣ ሠላምና ብልፅግና ያስፈልገኛል ብሎ ከፓርቲያችን እና መንግስታችን ጎን በመቆሙ ብቻ የጥፋት መንገድን በመረጡ ሃይሎች ሰቆቃና እንግልትን ሲያስተናግድ ቆይቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የተመኘውን ልማትና እድገት በምኞቱ ልክ ሳያገኝ ቆይቷል ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ።

የሰላም እጦት ያንገሸገሸው የወለጋ ህዝብ በዛሬው ዕለት ህዝባዊ ማዕበል በሚባል ደረጃ በነቀምቴ ስታዲየም በመገኘት የድጋፍ ሰልፍ ማድረጉን አውስተዋል፡፡

ይህም በመስዋዕትነት የተገኘውን ድልና ነፃነት በመጠበቅ፣ ሰላምና ልማትን ለማስቀጠልና የነገ ዕጣ ፋንታው የሚረጋገጥበትን የብልጽግና ግቦች ለማሳካት የበኩሉን ሚና ለመጫወት ቆርጦ መነሳቱን በተጨባጭ ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

በዚሁ የድጋፍ ሠልፍ በደምና በአጥንት፣ በሕይወት መስዋዕትነት ለገነባችሁት ስርዓት ያላችሁን ድጋፍ እና አብሮነት በማንፀባረቃችሁ ታላቅ ኩራት ተሰምቶኛል ብለዋል፡፡

ወለጋ የሠላም፣ የልማትና የብልፅግና ምድር ብቻ እንደሆነች በማረጋገጣችሁም ለእናንተ ያለኝ አክብሮትና አድናቆት ላቅ ያለ መሆኑን በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ከአራቱም የወለጋ ዞኖችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በነቂስ በመውጣት ለፓርቲውና ለመንግስት ያለውን ድጋፍ በአደባባይ ለገለፀው የወለጋ ሕዝብና አመራሮች አቶ ፍቃዱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

መስዋዕትነትን በመክፈል ሌት ተቀን ከህዝብ ጎን ለቆሙ የጸጥታ አካላት፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ለድጋፍ ሠልፉ መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ የተወጡ አካላትንም አመስግነዋል፡፡

በቀጣይ በጋራ በመሆን ሠላምና ፀጥታን በማጽናት የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት የሚረጋገጥበትን የብልፅግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ በጋራ እንቁም ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.