Fana: At a Speed of Life!

ከ10 ሀገራት የተውጣጡ ጀኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች የመከላከያ ተቋማትን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ10 ሀገራት የተውጣጡ 18 ጀኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች የመከላከያ ሚኒስቴርን ጨምሮ የመከላከያ ተቋማትን ጎበኙ፡፡

ጎብኚዎቹ ብሪታንያ ከሚገኘው ሮያል ኮሌጅ ኦፍ ዲፌንስ የመጡ ሲሆን÷ የግሎባል ስትራቴጂ ፕሮግራም ኮርስ ተማሪዎች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የመከላከያ ትምህርት እና ስልጠና ዋና መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን እና የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ ለጎብኚዎቹ ገለፃ አድርገዋል፡፡

የመከላከያ ዋር ኮሌጅን በጎበኙበት ወቅትም አሁናዊው የአፍሪካ ቀንድ የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ ምን እንደሚመስል በኮሌጁ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡

እንዲሁም የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ከጎበኙ በኋላ አጠቃላይ የአየር ኃይል እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል እና አየር ኃይሉ ለተቋሙ እያበረከተ ያለው ከፍተኛ ወታደራዊ አስተዋፅኦ ምን ያህል እንደሆነ በአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል በኩል ማብራሪያ ተሠጥቷል።

ጎብኝዎቹ ተቋሙን ለማወቅ እና ለመጎብኘት ላቀረቡት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ከመስጠት ጀምሮ ግልፅ ባልሆኑላቸው ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ እና በጉብኝቱ ዙሪያ ላነሷቸው ጥያቄዎችም ተገቢ መልስ በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ከ10 ሀገራት ከተውጣጡት መኮንኖች ጋርም ሆነ ከሮያል ኮሌጅ ኦፍ ዲፌንስ ጋር ጠንካራ ትብብርና ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በማንኛውም ወታደራዊ ጉዳዮች ላይም በትብብር መስራት አስፈላጊ ስለመሆኑም ውይይት መደረጉን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.