Fana: At a Speed of Life!

በኢስላማባድ የኢትዮ-ፓኪስታን የቢዝነስ ፎረም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከካራቺ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና ከኮራንጊ ንግድና ኢንዱስትሪ ማኅበር ጋር በመተባበር የኢትዮ-ፓኪስታን የቢዝነስ ፎረም አካሄደ፡፡

ፎረሙ የተካሄደው ከፈረንጆቹ ግንቦት 26 እስከ 31 ቀን 2024 ድረስ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገውን 2ኛው የንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ ጉብኝት አስመልክቶ መሆኑን የኤምባሲው መረጃ አመላክቷል፡፡

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር የካራቺ የንግድ ማኅበረሰብ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላው አፍሪካ ጋር የመገናኘት ልዩ ዕድል በሚፈጥረው 2ኛው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉብኝት ላይ እንዲሳተፍ ጋብዘዋል፡፡

ጉብኝቱ የአፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ ከመላው ዓለም የተውጣጡ አምራቾች በሚሳተፉበት በ6ኛው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ እና ቴክኖሎጂ ንግድ ትርኢት ላይ ለመሳተፍ እድል እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል፡፡

ልዑኩ በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የቢዝነስ ፎረሞች እና ውይይቶች እንደሚኖሩ ጠቁመው÷ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እና የቱሪስት መስኅቦችን የሚጎበኝበት ሁኔታ እንደሚኖርም አመላክተዋል፡፡

የካራቺ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢፍቲክሃር አህመድ ሼክ በበኩላቸው÷ 2ኛው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉብኝት ለካራቺ የንግድ ማኅበረሰብ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል ወደ አፍሪካ የሚገቡበት ጊዜ አሁን መሆኑን አንስተዋል፡፡

የከራንጊ ንግድና ኢንዱስትሪ ማኅበር ፕሬዚዳንት ሰይድ ጆሃር አሊ ቃንድሪ÷ 2ኛውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉብኝት በመቀላቀል የፓኪስታን ኩባንያዎች አዋጭ የሆነውን የኢትዮጵያ የንግድ ገበያ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.