Fana: At a Speed of Life!

ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ዝግጅት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ዝግጅት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በግብርና ሚኒስቴር ብሔራዊ የአረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር)እንደገለጹት÷ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለማዘጋጀት ርብርብ እየተደረገ ነው።

የዝግጅቱ 60 በመቶ ለፍራፍሬ፣ ለመኖና ለአፈር ለምነት ጥበቃ ጠቀሜታ ባላቸው ችግኞች  ላይ ሲሆን÷ 40 በመቶው ዝግጅት ደግሞ  ለውበትና ለደን ልማት አገልግሎት በሚውሉ ችግኞች ላይ ትኩረቱን ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

በእስከ አሁኑ ሂደትም በ102 ሺህ የመንግስት፣ የግልና የህብረት ስራ ማህበራት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

እየተዘጋጁ ከሚገኙ ችግኞች መካከል 6 ነጥብ 3 ቢሊየን የሚሆነው ተቆጥሮ ለተከላ እየተዘጋጀ መሆኑን የገለፁት ሰብሳቢው ÷ይህም በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከታቀደው በላይ ችግኝ እንደሚዘጋጅ አመለካች መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ለችግኝ ተከላ የሚውል 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለመለየት የታቅዶ እስከ አሁን ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት መለየቱን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአጠቃላይ የችግኝ ዝግጅቱና የተከላ ቦታ ልየታ ከ90 በመቶ በላይ መጠናቀቁንም አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.