Fana: At a Speed of Life!

አቶ ታዬ ደንደአ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ታዬ ደንደአ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡

ዋስትና ላይ የግራ ቀኝ ክርክር መርምሮ ብይኑን የሰጠው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ህገመንግስትና ህገመንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ታዬ ደንደአ ላይ ሦስት ክሶችን ማቅረቡ ይታወሳል።

ይኸውም ክስ፥ ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ የመንግስት እና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ፣ ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው ፀረ-ሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ መልዕክቶችን በስማቸው በተከፈተ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያስተላልፉ ነበር የሚል ነው፡፡

በተጨማሪም ተከሳሹ ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታኅሣስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5:00 ሰዓት ላይ በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ ከሁለት የክላሽንኮቭ ካዝና ከ60 ጥይት ጋር ይዞባቸዋል የሚል ነው።

አቶ ታዬ ከጠበቆቻቸው ጋር ችሎት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ ከደረሳቸውና በንባብ ከተሰማ በኋላ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጥያቄ ቀርቧል።

በዐቃቤ ሕግ በኩል የዋስትና ጥያቄያቸው በሰበር ሰሚ ችሎት ዋስትናን በልዩ ሁኔታ ሊከለክል የሚችልባቸው ነጥቦችን ማለትም በተደራራቢ ክስ መከሰሳቸውንና የተከሰሱበት ድንጋጌ ከፍ ያለ ቅጣት የሚያስጥል ከሆነ ዋስትና ሊያስከለክል ይችላል በማለት ተከራክሯል።

በተከሳሽ ጠበቆች በኩል ሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀመጣቸው ዋስትናን ሊያስከለክሉ የሚችሉ ድንጋጌዎች ተከሳሹ ላይ በቀረበው ክስ የሚመለከቱ አለመሆናቸው ጠቅሰው መልስ ስጥተዋል።

በተጨማሪም ህጻን ልጃቸውን ጥለው መታሰራቸውን ጠቅሰው፥ በህገመንግስቱ የተቀመጠው የህጻናት መብት ታሳቢ ተደርጎ በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱም ያቀረቡትን የዋስትና የመብት ጥያቄን መርምሮ ዛሬ በዋለው ችሎት አቶ ታዬ በወ/መ/ስ/ህ ቁጥር 67 መሰረት በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ብይን ሰጥቷል።

አቶ ታዬ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ላይ ዛሬ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ አስተያየቱን በጽሁፍ የሰጠ ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱም የክስ መቃወሚያው ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.