Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ አቅሞችን ወደ ስራ በማስገባት ተጨባጭ ለውጥ አስመዝግቧል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ አቅሞችን ወደ ስራ በማስገባት ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፤ በንቅናቄው አማካኝነት ባለፉት 9 ወራት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል።

ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ምቹ የሆነ እምቅ አቅም እንዳላት ጠቅሰው፤ ለኢንዱስትሪ ዋነኛ ግብዓት ከሆኑት መካከል ግብርና ዋነኛው በመሆኑ መንግስት የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ የቻሉ ሰፋፊ ስራዎችን አከናውኗል ነው ያሉት።

በስንዴ፣ ቡና፣ ሩዝና ሻይ ምርቶች ላይ የተከናወኑ ስራዎችንም ለአብነት አንስተዋል።

በተጨማሪ በኢነርጂና በሰው ሃይል ያሉ አቅሞችም ለኢንዱስትሪ ምርታማነት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እነዚህ አቅሞችን ወደ ስራ በማስገባት ረገድ ለውጥ እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረው፤ ለአብነትም ባለፉት 9 ወራት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል ብለዋል።

በቀጣይ በግብርና ምርታማነት ላይ የተመዘገበውን ስኬት መሸከም የሚችል የኢንዱስትሪ ልማት መገንባት ይገባል ነው ያሉት።

የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህልን ማዳበር እንደሚገባም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገለጹት።

በሚሊኒየም አዳራሽ የተከፈተው ይህ ኤክስፖ ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ 210 አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄው ሚያዚያ 2014 ዓም የተጀመረ ሲሆን እስከ 2024 ዓም ተግባራዊ እንደሚደረግ ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.