Fana: At a Speed of Life!

መገናኛ ብዙሃን የጋራ መገለጫዎችን በማጉላት የወል ትርክትን መፍጠር ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መገናኛ ብዙሃን የሕዝቦችን የጋራ መገለጫዎች አጉልቶ በማሳየት የወል ትርክትን መፍጠር ላይ በትኩረት መስራት አለባቸው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዳንኤል ክብረት ገለጹ፡፡

አማካሪ ሚኒስትሩ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት “መገናኛ ብዙሃን ለጋራ ትርክት ግንባታ የሚኖረው ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተገኝተው ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

በመድረኩም የኢትዮጵያ ህዝቦች ለረዥም ዘመናት በአብሮነት የኖሩባቸው እና የሚያስተሳስሯቸው የጋራ ባህል እና እሴቶች እንዳሏቸው አውስተዋል፡፡

ለአብነትም በየትኛውም አካባቢ በሚከናወኑ ባህላዊ ክዋኔዎች ላይ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው እሴቶች መኖቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህን የጋራ መገለጫዎች አጉልቶ በማሳየት የወል ትርክት መፍጠር ላይ ውስንነት መኖሩን ነው ያስገነዘቡት፡፡

መገናኛ ብዙሃን ከሊሂቃን ባለፈ ሕብረተሰቡ በጋራ ተከባብሮ እና ተሰናስሎ ለመኖር ያስቻለውን ማህበራዊ መስተጋብር እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ሃሳቡን እንዲያካፍል የማድረግ ልማዳቸው ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ስለሆነም መገናኛ ብዙሃን የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት የሚያንጸባርቁ ነባር የጋራ ባህላዊ መስተጋብሮችን ወደ ፊት በማምጣት የወል ትርክት መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት፡፡

በተለይም በህዝቦች የጋራ ባህሎች፣ ማህበራዊ እሴቶች፣ ሀገርን ለመከላከል ያላቸውን ጀግንነት፣ አንዱ ማህበረሰብ ሌላውን የሚቀበልበት መንገድና ሌሎች እሴቶችን በሚገባ ማሳየት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በህዝቦች ባህላዊ አስተራረስ፣ አልባሳት፣ ምግብ አሰራር፣ በንግድ ልውውጥ እና ሌሎች አጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ ያሉ የጋራ እሴቶችን ነቅሶ በማውጣት ለህብረተሰቡ ማሳወቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች የጋራ የሆኑ መገለጫ ሃብቶችን በሚገባ በማሳየት የወል ትርክትን መገንባት ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ስንቅ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ እና ሃይለኢየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.