ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከሳዑዲ ዓረቢያ የመንግስትና የንግድ ልዑካን ቡድን አባላት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘዉዴ ከሳዑዲ ዓረቢያ የመንግስትና የንግድ ልዑካን ቡድን አባላት ጋር ተወያይተዋል።
ልዑካኑ በውይይታቸው በኢትዮጵያ እየታየ ያለዉ ለዉጥ ለንግድና ኢንቨስትመንት አመቺ ሁኔታ የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም በብዙ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው መግለፃቸውን ከፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በበኩላቸው የሳዑዲ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በሚያደርጉት የቢዝነስ እንቅስቃሴ ሁሉ መንግስት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያድርግ ተናግረዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አህመድ አል ቃጣን የሚመራውና ሃምሳ አባላት ያሉት የሀገሪቱ መንግስትና የንግድ ልዑካን ቡድን የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ባሳለፈነው ዕሁድ አዲስ አበባ መግባቱ ይታወሳል።
በቆይታውም ከተለያዩ የመንግስት አካላትና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ አባላት ጋር የኢትዮጵያና የሳዑዲ ዓረቢያን ሁለንተናዊ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ እየመከረ ይገኛል።