ዴንማርክ ለቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ተፈራረመች
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዴንማርክ ቀጣዩን ሃገራዊ ምርጫ ለመደገፍ የሚውል የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመች።
የድጋፍ ስምምነቱን በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ካሪን ፖልሰን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካይ ቱርሃን ሳልህ ተፈራርመውታል።
የዛሬው ስምምነት የዴንማርክ የትብብር ሚኒስትር ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የዴንማርክ መንግስት በገባው ቃል መሰረት የተደረገ ነው ተብሏል።
አምባሳደር ፖልሰን በኢትዮጵያ የሚደረገው ምርጫ ሃገሪቱ ወደ ሰላምና ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህ አንጻርም ሃገራቸው ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ትሰራለች ብለዋል።
ድጋፉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማጠናከር ለሚያካሂደው ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ነው ተብሏል።
ፕሮጀክቱ ከፈረንጆቹ ከ2019 እስከ 2022 የብሄራዊ የምርጫ ቦርድን አቅም ለመገንባት የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ ግልፅ፣ ነጻ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ ምርጫን ማካሄድ፣ የህዝብ ተሳትፎን ማሳደግ፣ በምርጫ ወቅት የሚነሱ ግጭቶን ቀድሞ በመለየትና በመቆጣጠር ምላሽ መስጠት የሚቻልበትን አግባብ መፍጠርን አላማው ያደረገ ነው።
መረጃው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ነው።