Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 3 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ክልላዊ የሁኔታ ግምገማ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በመነጋገር ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ፡፡

ኦሮሚያ ብልጽግና ከፍተኛ አመራሮች ኮንፈረንስ አጠቃላይ የለውጡን ሂደት ጠንካራና ደካማ ጎኖችን የገመገመ ሲሆን ለውጡን ለመቀጠል የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ መጠናቀቁን የክልሉ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ማምሻውን ገልጸዋል፡፡

ኮንፈረንሱ በሁለት ቀናት ቆይታው የለውጡን ሂደት ሲገመግም ከለያቸው ጠንካራ ጎኖች መካከል የለውጥ አመራሩ ሀገሪቱን ከተረከበ ጀምሮ ሀገሪቱን ከብተና ማዳን መቻሉ፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋቱ፡ የውይይትና የክርክር ባህል እንዲዳብር የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠር የተደረገው ጥረት እንደአብነት መነሳቱን አቶ ፍቃዱ ገልጸዋል፡፡

ከኢኮኖሚ አንጻርም እስከዛሬ ድረስ የአርሶ አደሩን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ ትልልቅ እርምጃችን የወሰደ ሲሆን በገጠር ፋይናንሲንግ ስርዓት አርሶ አደሩን በቀላሉ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉ፡ እንዲሁም የግብርና ግብዓት አቅርቦቶችና የመሳሰሉት ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መደረጉ፡ አርሶ አደሩ ምርቱን በቀላሉ ለገበያ እንዲያቀርብ የሚያደርግ አስቻይ ሁኔታ መፈጠሩ እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል መሆኑ በኮንፈረንሱ ተገልጿል፡፡

የለውጥ አመራሩ የህዳሴ ግድብ የነበረበትን ችግር በመገምገምና በማስተካከል ካለበት ችግር ተላቆ ወደ ውጤት እንዲመጣና የግድቡ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት በድል እንዲጠናቀቅ ማድረጉም ታይቷል፡፡

በተጨማሪም የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝና መላው ህዝቦች በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተሳትፏቸውን አጠናክረው የቀጠሉ መሆኑን ኮንፈረንሱ የገመገመ ሲሆን፡ ይኸው ተጠናክሮ ለዘላቂ ልማት ስኬት በሚረዳ መልኩ እንዲቀጥል አቅጣጫ ማስቀመጡን አቶ ፍቃዱ ተሰማ ገልጸዋል፡፡

ኮንፈረንሱ በቆይታው ከውስጥም ከውጭም የተለያዩ ትንኮሳዎችና ተጨባጭ የጥፋት ድርጊቶች በዓላማ በተሳሳሩ ድርጅቶችና ቡድኖች እየተፈጸሙ እንዳሉና፡ ይህንንም ከመላው ህዝብ ጋር በመሆን እያከሸፈ ትግሉን የሚቀጥል መሆኑን ገልጾ፡ የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎችም በዋናነት ህወሃትና የኦነግ ሸኔ ቡድን መሆናቸውን ተመልክቷል፡፡

ይህም በህይወት መጥፋትና በንብረት ውድመት፡ ዜጎች ያፈሩትን ሀብትና ንብረት በማውደም፡ መሰረት ልማቶች ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ፡ ኢንቨስትመንትን እንዲዳከም ምክንያት በመሆን እንደሚገለጽ ኮንፈረንሱ በስፋት አይቷል፡፡

ኮንፈረንሱ በተጨማሪም ሁለት ቦታ የቆሙ አመራሮች መኖራቸውን የተገነዘበ ሲሆን መረጃ በመስጠት፡ ከሌላ ሃይል ጋር በመስራት፡ ሙስና እንዲስፋፋ በማድረግ የተሰለፉ አመራሮችን የማጥራት እርምጃ መውሰዱንም አቶ ፍቃዱ ገልጸዋል፡፡

በዚሁም መሰረት ሶስት የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ከፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የታገዱ ሲሆን፡ እነሱም አቶ ለማ መገርሳ፣ ወይዘሮ ጠይባ ሃሰንና ዶክተር ሚልኬሳ ሚደጋ እንደሆኑ ይፋ አድርጓል፡፡

አቶ ለማ መገርሳ እንዲታገዱ የተደረገው የፓርቲ ዲሲፕሊን መጠበቅ ባለመቻል፣ ልዩነትን በፓርቲ መድረክ ከማቅረብ ይልቅ ከዚህ በተቃራኒው ሌሎች መንገዶችን እንደ አማራጭ መውሰዳቸውና ይህንኑ ለመፍታት ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላም በፓርቲው መድረኮች ላይ እና በመደበኛ የስራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘታቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ዶክተር ሚልኬሳ ሚዳጋም በተመሳሳይ ለሚያነሱት ሃሳብ የፓርቲውን መድረኮች  ከመጠቀም ይልቅ ሌሎች ከፓርቲው ዲሲፕሊን ውጪ የሆኑ አማራጮችን በመጠቀማቸውና የፓርቲውን ምስጢር ለሌሎች ሃይሎች አሳልፎ በመስጠት ተገምግመው ውሳኔው እንደተላለፈባቸው ተመልክቷል፡፡

ወይዘሮ ጠይባ ሃሰን ደግሞ በቅርቡ በምዕራብ አርሲ ተከስቶ ከነበረው የሰላም መደፍረስ ጋር በተያያዘ የሚነሱባቸው ችግሮች በመኖራቸው፣ የፓርቲውን ምስጢር ለሌላ ወገን አሳልፎ በመስጠት እንዲሁም በፓርቲው መድረኮችና በመደበኛ ስራቸው ላይ ባለመገኘታቸው እገዳው እንደተላለፈባቸው በኮንፈረንሱ ነው የተመለከተው፡፡

ይህም ውሳኔ በፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

የተወሰደው እርምጃ ከፓርቲው አሰራር አንጻር ሲሆን ህጋዊ ጉደዮችን በተመለከተ በመደበኛ የህግ አግባብ የሚታይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምንም እንኳ የተለያዩ ተግዳሮቶች እየገጠሙት ቢሆንም የጀመረውን የልማት፣  የሰላም እና የለውጥ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና የህዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚሄድ የጽህፈት ቤት ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.