በህንድ ከዜግነት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በተነሳው ተቃውሞ 9 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህንድ በቅርቡ የወጣው አዲሱ የዜግነት ህግ ሙስሊሙን ማህበረሰብ ያገለለ ነው በሚል በሀገሪቱ በተቀሰቀሰው ታቀውሞ በርካቶች መገደላቸው ተገለፀ፡፡
ለህንድ ፓርላማ የቀረበው የዜግነት ህግ መገለል ይደርስባቸዋል የተባሉ እና ሙስሊም ያልሆኑ የአፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን እና ባንግላዲሽ ዜጎች የህንድ ዜግነት እንዲያገኙ የሚፈቅድ ነው።
ውሳኔን ተከትሎም ከሀገሪቱ ዜጎች 14 በመቶ የሚሸፍኑትን የሙስሊም ማህበረሰቦች በማግለል የሂንዱን እምነት የበላይነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው በሚል ተቃውሞው በርትቷል፡፡
በዚህ የዜግነት ህግ የተቆጡ ህንዳውያን በመንግስት የተጣለውን ገደብ ውድቅ በማድረግ በተለያዩ ከተሞች ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ሳቢያም እስካሁን 9 ሰዎች መሞታቸው ነው የተነገረው።
ማንጋሎሬ በተባለች ከተማ በነበረው ተቃውሞም ሁለት ሰዎች መሞታቸውን የሆስፒታል ምንጮች ገልጸዋል።
የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ጉዳት ያጋጠማቸው ሌሎች አራት ሰዎች ማንጋሎሬ በሚገኘው ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል ተብሏል፡፡
200 የሚሆኑ ሰዎች የተቃውሞ ሰልፉን እንዲያቋርጡ በፖሊስ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ፖሊስ ተኩስ መክፈቱ ነው የተነገረው፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ አቅራቢነት የወጣው አዲስ ህግ በመላ ሃገሪቱ መጠነ ሰፊ ተቃውሞን አስነስቷል።
ምንጭ፡- አልጀዚራ