ደም ሳይቃቡ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ያስፈልጋል – ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 10 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት በሚሊኒየም አዳራሽ የአማራ እና የኦሮሞ ባለሃብቶች ኮሚቴ ባዘጋጁት የሰላም ኮንፈረስ ላይ ንግግር አድርገዋል።
በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዚህ አይነት መድረኮች እንዲዘጋጁ ድጋፍ ላደረጉ ምሁራን፣ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ባለሀብቶች ምስጋና አቅርበዋል።
እንዲሁም በሀገሪቱ የሰላም አየር እንዲመጣ እና ሰዎች ሀሳባቸውን በነፃነት ማንሸራሸር እንዲችሉ ድጋፍ ያበረከቱ ቄሮዎችና ፋኖዎችን አመስግነዋል።
የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦች በርካታ ቁጥር ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በጋራ ሲሆኑና ሲተባበሩ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ እና በተቃራኒው ሲለያዩ የሚለውጡት ነገር እንደማይኖር ገልፀዋል።
ሁለቱ ብሄሮች በሃገሪቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ መዋደድ፣ መከባበር እና መፋቀር እንደሚገባቸውም አውስተዋል።
በቀጣይነት ሁለቱም ህዝቦች በሁሉም አቅጣጫ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ ውይይቶችን እንደሚያዘጋጁ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ልዩነት ፀጋ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሻለና የተለያየ ነገር ያስፈልጋልም ብለዋል በንግግራቸው።
አብሮ ለመኖርም የአብሮ መኖር ጥቅምን መገንዘብ፣ የሌሎችን እሴት ማወቅ እና ሳይጠፋፉ አብሮ መኖር እንዴት ይቻላል የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል ሲሉም ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብሮ ሲኖር የሃሳብ ግጭት አይኖርም ማለት ሳይሆን በዚህ የሀሳብ ልዩነት መገዳደልና መጠፋፋት አያስፈልግም ማለት መሆኑንም አስረድተዋል።
ወጣቶች የታገሉት፣ የደሙት እና የደከሙት ተጨማሪ ወጣት እንዳይሞት እንጅ ሊማር የሄደ በወጣበት እንዲቀር ባለመሆኑ የአማራና የኦሮሞ ወጣቶች ተቀራርበው መስራት እንደሚገባቸው አስታውሰዋል።
ዩኒርሲቲዎችን በተመለከተም ባስተላለፉት መልዕክት ዩኒቨርሲቲ የሚኬደው ለመገዳደል ሳይሆን ለመማር መሆኑን ጠቅሰው፥ እነዚህን ወጣቶች ለግጭት የሚጠቀሙ አካላት እንደማይጠፉ አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ጠንካራ ጥበቃ የማደራጀት ስራ መከናወኑን እና በጥፋተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለዴሞክራሲያ ሽግግር ባደረጉት ንግግር ሰላም እንዲሰፍንና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ደም መቀባባት እንደማያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ወጣቶችም አሁን ካሉበት ቦታ በላይ እንዲያስቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።