Fana: At a Speed of Life!

ኤጀንሲዉ በሳይበር ደህንነት ኦዲት 31 የሚሆኑ ተቋማት ላይ የተለያዩ የሳይበር ደህንነት ክፍተቶች መለየቱን ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 5 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በ2012 የበጀት አመት ባደረገዉ የሳይበር ደህንነት ኦዲት 31 የሚሆኑ ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት መለየቱን እና እንዲታረሙ ማድረጉን ገለጸ።

በኤጀንሲዉ የሳይበር ደህንነት ኦዲት እና ኢቫልዌሽን ዲቪዥን ሀላፊ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ወ/ጊዮርጊስ÷ በተጠናቀቀዉ የ2012 በጀት አመት ኤጀንሲው በ31 የመንግስት እና የግል ተቋማት ላይ ጥልቅ የደህንነት ፍተሻዎችን ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም የደህንነት ኦዲት የተደረገላቸው ሁሉም ተቋማት ክፍተት እንደተገኘባቸዉ የተናገሩት ሀላፊው ÷ ተቋማቱ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን አንስተዋል።

ይህም ማለት ክፍተት ያለበት ሲስተም ወይም የሳይበር መሰረተ-ልማት ፣ የሰው ሃይል እና የሳይበር ደህንነት አስተዳደር ሂደት መሆኑን ጠቁመዋል።

በተቋማቱ ላይ በስፋት ከተገኙት የሳይበር ደህንነት ክፍተቶች መካከል፣ በሲስተሞች እና የሳይበር መሰረተ-ልማት ግንባታ ላይ የሚፈጠሩ ቴክኒካዊ ክፍተቶች፣ ተቋማት የራሳቸው የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ አለመኖር እና ፖሊሲዉ ያላቸዉ ቢሆኑም በተገቢው መንገድ ተግባራዊ አለማድረግ እንዲሁም የተቋማቱ የበላይ አመራሮች ለሳይበር ደህንነት የሚሰጡት ዝቅተኛ ግምት ዋንኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አቶ ደሳለኝ ተነግረዋል።

ከተለዩት የሳይበር የደህንነት ክፍተቶች መካከል 56 በመቶ የሚሆኑት ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ሲሆን 35 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በመካከለኛ ደረጃ እንዲሁም 9 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳታቸው ዝቅተኛ የሚባሉ ናቸዉም ነው ያሉት።

ሃላፊው አያይዘውም እነዚህን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነቶችን ለመቅረፍ ተቋማቱ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባቸዉ አሳስበዋል።

ከእነዚህ የጥንቃቄ መንገዶች መካከልም በኤጀንሲዉ የተሰጣቸውን ምክረ ሃሳብ መሰረት በማድረግ ክፍተቶቹን ማስተካከል፣ ማንኛውም ሲስተም ወይም የሳይበር መሰረተ-ልማት ከመተግበሩ በፊት የደህንነት ፍተሻ እንዲደረግለት ማድረግ፣ ከኤጀንሲው ጋር ተቀራርቦ መስራት እና አስፈላጊውን እገዛ መጠየቅ ፣ተቋማት አገልግሎት እየሰጡበት የሚገኙትን የሳይበር ስርዓቶች ቢያንስ በዓመት አንዴ የደህንነት ፍተሻ እንዲደረግላቸው ማመቻት ይገባቸዋል ማለታቸውን ከኢመደኤ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.