የከተማዋን ሰላም ለማደፍረስ የተለያየ የሽብር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል-ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህዝብና መንግስት ላይ በፈጠሩት ክህደትና የከተማዋን ሰላም ለማደፍረስ የተለያየ የሽብር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ 10 የሚሆኑ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በመግለጫቸው በከተማው ውስጥ የተለያዩ ህገወጥ መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ህብረተሰቡ የጥፋት ሃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ በአንድ ቀን ከ2000 በላይ ጥቆማዎች በመስጠት ላይ መሆኑን ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ፣በየመጋዘኑ ምርትን በመደበቅ በሌሎች ህገወጥ ተግባራት የተሰማሩ 25 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን እና የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው በመግለጫው ማንሳታቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በከተማዋ የጸጥታ ሁኔታው በተጠናከረ መንገድ እየተሰራ እንደሚገኝ በመግለፅ ከ880 በላይ የብሎክ አደረጃጀቶች አማካኝነት በየሰአቱ ከነዋሪያችን እና ከፀጥታ ሃይሉ እንዲሁም ከኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ምክትል ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡
በመንግስታዊ ተቋማት መደበኛ አገልግሎቶች በተገቢው ሁኔታ እንዲሰጥ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ወይዘሮ አዳነች የገለጹ ሲሆን፥ ህብረተሰቡም መብቱን የማስከበርና ግዴታውን የመወጣት እንቅስቃሴውን ማስቀጠል ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡