በትግራይ ክልል የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በሚነዙ መገናኛ ብዙኀን ላይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል – አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል የሐሰት ፕሮፓጋንዳ የሚነዙና በህዝቡ ውስጥ ውዥንብር የሚፈጥሩ መገናኛ ብዙኀን ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሳሰበ።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመጠቀም ከህገ-መንግሥቱ ጋር በሚቃረን መልኩ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠርና አገር እንዲተራመስ በሚሰሩ መገናኛ ብዙኀን ላይ ቁጥጥር እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።
አፈ ጉባኤው “ህገ-መንግሥታዊ መብት በሚጥስ መልኩ በሚንቀሳቀስ የመገናኛ ብዙኀን ተቋም ላይ ተገቢ እርምጃ ሊወሰድ ይገባልም” ብለዋል።
ሥልጣን የተሰጣቸው ተቋማት ህገ-መንግሥቱንና መገናኛ ብዙኀን አስመልክቶ የወጡ ህጎች አፈጻጸምን በመከታተል ጥሰት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ ነው ያሳሰቡት።
አፈጉባኤው በህገ-መንግሥቱ መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲዳብር ይሠራል ነው ያሉት።
ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ የትምህርት ተቋማትና መገናኛ ብዙኀን ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አፈ-ጉባኤው መገናኛ ብዙኀን የጋራ ማንነት ለመፍጠር መሥራት እንደሚገባቸው ጠቁመው፣ ከዚህ በተቃራኒ የሚሰሩ ካሉ ተገቢ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።