ጠ/ሚ ዐቢይ የምዕራቡ የትግራይ ክልል ቀጠና ነጻ መውጣቱን አስታወቁ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሃገር መከላከያ ሰራዊት በወሰደው እርምጃ የምዕራቡ የትግራይ ክልል ቀጠና ነጻ መውጣቱን አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ በዚያ ቀጠና ሠራዊቱ ሰብአዊ እርዳታና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ነጻ ባወጣቸው አካባቢዎች ሕዝቡን እየመገበ፣ እያከመና እየተንከባከበ ነው ብለዋል፡፡
ለስግብግቡ ጁንታ ግፍ እስትንፋሱ፣ ጭካኔ ነፍሱ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ሽራሮን ሲቆጣጠር፣ እጅና እግራቸውን የፊጥኝ ታሥረው የተረሸኑ የመከላከያ አባላትን ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡
ጭካኔው ልብ ሰባሪ እንደነበር በማውሳትም ዓላማው ኢትዮጵያን መስበር እንደሆነም አንስተዋል፡፡
በፅሁፋቸው ኢትዮጵያ ከአልማዝ የጠነከረች መሆኗን አላወቁም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ የጁንታው ዓላማ ሠራዊቱንና ሕዝቡን አስቆጥቶ ለበቀል እርምጃ ማነሣሣት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያም ልበ ሰፊ ሕዝብና ሠራዊት አላትም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በየቦታው ከዚህ የከፋ ጭካኔና ግፍ ሊያጋጥም እንደሚችል በመጥቀስም የአሁኑ ግን ለዚህ ጁንታ የመጨረሻው መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ጥንቃቄው ሙት ይዞ እንዳይሞት በመሆኑ፥ በመፍጠን የተረፉትን መታደግና ግፍ የተፈጸመባቸውንም ለዓለም ለማጋለጥ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡