የህዝብ መገልገያዎችን ማውደም የህዝብ ጠላት መሆንን የሚያረጋግጥ ነው – የጉጂ አባገዳዎች
አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በከፍተኛ ወጭ የተገነቡትን የህዝብ መጠቀሚያ የመሰረተ ልማቶችን ማውደም የህዝብ ጠላት መሆንን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ የጉጂ ኦሮሞ አባገዳዎች ተናገሩ።
አባገዳዎቹ የህወሃት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ የፈፀመው ጥቃት አስነዋሪ ተግባር ነው።
በህወሃት ቡድን ላይ መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ ተከትሎ ቡድኑ ተስፋ ቆርጦ የህዝብ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል።
ቡድኑ የአየር ማረፊያን ጨምሮ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን ማፍረሱ የህዝብ ጠላት መሆኑን የሚያረጋግጥ እኩይ ተግባር መሆኑን አባገዳዎቹ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
አባገዳ ጊርጆ ጎዳና ትናንት ኢትዮጵያን ሲጎዱ የነበሩ አካላት አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ የአገርና የህዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶችን ማውደማቸው ደግሞ ከጥፋትም ጥፋት መሆኑን ገልጸዋል።
አባገዳ ቦኮ ገናሌ በሰጡት አስተያየትም “የህወሃት አጥፊ ቡድን ያፈረሳቸው መሰረተ ልማቶች በህዝብ ገንዘብ የተገነቡ የህዝብ ሃብቶች በመሆናቸው ሁላችንንም አሳዝኖናል” ብለዋል።
በመሆኑም እነዚህ አጥፊዎች ተይዘው በህግ ተጠይቀው መቀጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የህወሃት ቡድን የትግራይን ህዝብ ምሽግ በማድረግ “ተወረሃል፣ ተከበሃል” በሚል እያሳሳተ አገር ለማፍረስ መነሳቱም ሁሉንም ያሳዘነ ድርጊት መሆኑን አባገዳዎቹ ገልጸዋል።
መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደ የሚገኘው የህግ ማስከበር ዘመቻ ሀገርና ህዝብን ለመታደግ በመሆኑ ተገቢ ነው ብለዋል።