Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ በቀጣዩ ወር የኮሮና ቫይረስ ክትባት ልትሰጥ እንደምትችል አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካውያን በቀጣዩ ወር የኮሮና ክትባት ሊያገኙ ይችላል ተባለ፡፡

የኮሮና ቫይረስ መርሃ ግብር የክትባት ሃላፊ ዶክተር ሞንሴፍ ስሎይ አሜሪካ በፈረንጆቹ ታህሳስ 11 ቀን ለዜጎቿ ክትባት ልትሰጥ ትችላለች ብለዋል፡፡

ይሰጣል የተባለው ክትባት ፋይዘር በተባለው መድሃኒት አምራች ኩባንያ የተመረተ ሲሆን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እውቅና ይሰጠው ዘንድ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

ሃላፊውም መድሃኒቱ እውቅና በተሰጠው በ24 ሰአታት ውስጥ ክትባቱን ለመስጠት እቅድ መያዙን ነው የተናገሩት፡፡

ፋይዘር ከጀርመኑ ባዮንቴክ ጋር ያመረተው ይህ መድሃኒት ፈዋሽነቱ 95 በመቶ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡

የአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር አማካሪ ምክር ቤትም ከሁለት ሳምንታት በኋላ ስብሰባ ይቀመጣል ነው የተባለው፡፡

መፍሃኒቱ በምክር ቤቱ እውቅና ካገኘም የመጀመሪያው አሜሪካዊ ታህሳስ ወር ላይ ክትባቱን የሚያገኝ ይሆናል፡፡

እስካሁን በአሜሪካ ከ12 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤ ከ255 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ለህልፈት መዳረጋቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያመላክታል፡፡

ዓለም ላይ ደግሞ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ59 ሚሊየን በላይ ሲሆን፤ በቫይረሱ ሳቢያ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥርም ከ1 ሚሊየን 393 ሺህ በላይ ደርሷል፡፡

በአንጻሩ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ከ40 ሚሊየን 776 ሺህ በላይ መሆኑን ነው መረጃው የሚያመለክተው፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ እና ዎርልድ ኦ ሜትር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.