Fana: At a Speed of Life!

መንግስት እና ህወሓት በተመሳሳይ ሚዛንና እኩል ስነ ምግባር የሚቀመጡ አይደሉም- አቶ ሀይለማሪያም

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 15 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት በተመሳሳይ ሚዛንና በእኩል ስነ ምግባር የሚቀመጡ አይደሉም ሲሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ገለፁ።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም በዛሬው ዕለት በፎሬን መፅሔት ላይ ሰፋ ያለ ፅሁፍ አስነብበዋል።

አቶ ሀይለማሪያም በፅሁፋቸው በርከት ያሉ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ትንታኔ የሚሰጡ እና የአፍሪካ ቀንድ ባለሙያ የተባሉ አካላት ሁሉንም አቀፍ ብሄራዊ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ በማቅረብ ላይ ተጠምደዋል ይላሉ።

እንዲሁም መንግስት በህወሓት ውስጥ ባለው ቡድን ላይ እየወሰደው የሚገኘውን ህግን የማስከበር እርምጃ እንዲያቋርጥ ጥሪ በማቅረብ ላይ መሆናቸው አንስተዋል።

ይህም ፊት ለፊት ሲያዩት መልካም ሀሳብ እንደሚመስል ጠቅሰው ከምንም ቢነሱም የሰላም ጥሪያቸው ግጭትን ለመፍታት እንደሆነ በፅሁፉ ላይ አብራርተዋል።

ይህን ምክረ ሀሳብ የሚሰጡ ሰዎች በደንብ አስበውበት በአፍሪካ ችግሮች የሚፈቱበትን የተለመደ መንገድ የማስተጋባት ልምድ እንዳላቸው እንደሚያምኑም ገልፀዋል።

የዓለም መንግስታት የተሳሳተ ሚዛን እንዲኖራቸው ያደረገውም መንግስትን እና ህወሓትን ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ በእኩል ስነ ምግባር ማየቱ መሆኑን አውስተዋል።

ሚዛናዊነት የሚጎድላቸውን እንዲህ አይነት ሀሳቦች በአንድ መጠቅለል አይሰራም ያሉት አቶ ሀይለማሪያም ለዚህም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የደቡብ ሱዳንን ችግር ያየበት መንገድ ጥሩ ማሳያ እንደሆነ አንስተዋል።

ደቡብ ሱዳን ነፃ ሀገር ከሆነች በኋላ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የተካሄደው የሰላም ውይይት ከስልጣን መጋራት ባሻገር ምንም ጉዳይ አለማካተቱን በማንሳት ስምምነቱ በግጭት ወቅት ለተፈጠረው የጅምላ ግድያ ተጠያቂነትን ያላሰፈነ ነው ብለዋል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቁልፉ ችግር በደቡብ ሱዳን የነበረውን አካሄድ በኢትዮጵያ ለመድገም መንግስት እና ህወሓትን ሚዛናዊነት በጎደለው መልኩ በእኩል ስነ ምግባር በማስቀመጥ የዓለም ሀገራት የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረጋቸው እንደሆነም ነው ያሰፈሩት።

ለ27 ዓመታት በህወሓት የበላይነት ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ ኢኮኖሚው እና ፖለቲካውን በተገቢው መንገድ ባለመምራቱ በህዝባዊ አመፅ የአመራር ለውጥ መምጣቱን አስታውሰዋል።

ነገር ግን አሁን ላይ ህወሓት ስትራቴጂ በመቀየስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሳተ ሚዛን እንዲይዝ በማድረግ ሌላ ግንዛቤ ለመፍጠር እና ድርድር እንዲኖር ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

የህወሓት አመራሮቹ ዓለም አቀፉን ማህረሰብ እንዴት ማጭበርበር እንደሚችሉ ያውቃሉ በማለትም ገልፀዋል።

የዚህ ቀመር ዋነኛ አካልም ከፌደራል መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባት በባለፈው እና በአሁኑ ጥፋታቸው ተጠያቂ ላለመሆን እና ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎችን በማስገባት ስልጣን መጋራት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ለዚህም የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀርፀው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጠቁመዋል።

የህወሓት አመራሮች አሁን በእቅዱ መሰረት እየሄደላቸው የሚገኘው በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ ሰዎች በኩል በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ውይይት እንዲደረግ እያሰሙት የሚገኘው ጥሪ ነው ብለዋል።

እነዚህ አካላት ከዚህ ተግባራቸው ባሻገር የህወሓትን ማኬቪሊያዊ እና የሰዎችን ህይወት የሚያጠፋውን አካሄድ ሲወቅሱ እንደማይታዩም ነው ያነሱት።

እንዲሁም በኢትዮጵያ ሰላምን እና መረጋጋት እንዳይፈጠር ሲንቀሳቀሱ እነዚህ አካላት ህወሓትን ለመውቀስ አይደፍሩም ነው ያሉት።

ከህወሓት ጋር ዓለም አቀፍ ስምምነት መድረስ የሀገሪቱ የፍትህ ስርዓት እና ቀጣይነት ያለው ሰላምን የማረጋገጥ ሂደትን በእጅጉ ይጎዳል ያሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ይህ አይነቱ አካሄድ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ለሌሎች ቡድኖችም የተሳሳተ ትምህርት ይሰጣልም ብለዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በፅሁፋቸው የፌደራሉ መንግስት ህግን የማስከበር እርምጃውን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንዳለበት እና የሰብዓዊ ጉዳቱን መቀነስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እንዲሁም የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት በመጠበቅ የህወሓት አመራሮችን ለፍትህ ማቅረብ እንደሚገባም ነው በፅሁፋቸው ያነሱት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.