Fana: At a Speed of Life!

በህግ ማስከበር ሂደት ለተፈናቀሉና በተለያዩ አደጋ ውስጥ ላሉ ወገኖች ድጋፍ የማድረስ ስራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተለያዩ አካባቢዎች በህግ ማስከበር ሂደት ለተፈናቀሉና በተለያዩ አደጋ ውስጥ ላሉ ወገኖች ድጋፍ የማድረስ ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የአደጋ ስጋት መከላከል ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በስራ አፈጻጸም ሂደቱ ላይ ለተሳታፊ ቡድን አባላት የሥራ መመሪያና አቅጣጫ ሰጥተዋል።

ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ቀናት ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሂደቱን እንዲያስተባብሩና እንዲመሩ እየተሰማሩ ያሉ ቡድኖች የአደጋ ስጋትና መከላከል ቡድን ማህበረሰቡን መልሶ ለማቋቋም፣ የጤና አገልግሎት ለማመቻቸት፣ የትራንስፖርት ሂደቱንም ለማስተካከል ጊዚያዊ የምግብና ውሃ አቅርቦት ለማሰናዳት እና የህዝብ የአገልግሎት ተቋማት ወደ ስራቸው እንዲገቡና ህብረተሰቡም ወደ እለት ተእለት ኑሮው እንዲመለስ በማስቻሉ ሂደት ላይ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ወደ ቦታው ካመሩት የቡድኑ አባላት በተጨማሪ በነገው እለት አምስት ቡድኖች ወደ ስፍራው ያቀናሉም ብለዋል፡፡

እነዚህ ቡድኖችም ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ሙያተኞች ሲሆኑ ከሰላም ማኒስቴር፣ ከሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች፤ ከውሃ ስራ፣ ከጤና፣ ከግብርና፣ ከትራንስፖርት እና ከንግድና እንዱስትሪ የተዋቀሩ ናቸው ተብሏል።

በዚህም አደጋውን ለመከላከል በተለያዩ አምስት አማካይ ጣቢያዎች ማለትም በጎንደር፣ዳንሻ፣ ማይካድራ፣ ባዕከር እና አዲ ረመጽ መቀመጫቸውን በማድረግ በሁሉም ስፍራዎች የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት እንደየክብደቱ እንዲዳረስ አፋጣኝ ስራዎች ይሰራሉ መባሉን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.