Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ግብርና ያሉበትን መሰናክሎች እንዴት ይለፋቸው?

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም ባንክ የማዕከላዊ ስታትስቲክስን መረጃ ዋቢ አድርጎ ባወጣው መረጃ  በኢትዮጵያ ግብርና  የስራ እድል በመፍጠር 70 ከመቶ በላይ ድርሻን ይዟል።

ሀገሪቱ ካላት የቆዳ ስፋት  እና በእርሻ መልማት ከሚችለው ጠቅላላ መሬቷ አሁን ላይ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው አናሳ ነው።

በተቃራኒው አሁንም ድረስ ለዳቦ የሚሆን ስንዴ በየዓመቱ ከግማሽ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ እያወጣች ከውጭ ታስገባለች።

በቅርቡ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለፋና ብድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳረጋገጠው ከጥቅምት ወር ጀምሮ በየወሩ 650 ሺህ ኩንታል የዳቦ ስንዴ በግዥ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል።

የግብርናው ምርታማነት ለምን ረዥም ርቀት መጓዝ ተሳነው?

ዶክተር በላይ ስማኔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሀገር ልማት ኮሌጅ ውስጥ የግብርና እና አየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተመራማሪ እና መምህር ናቸው፤ የግብርናው ዘርፍ ለምን አልተለወጠም በሚለው ላይ የጋራ መግባባይ ይጠይቃል ይላሉ።

ከአሁን በፊት በዘርፉ ላይ ብዙ ውይይቶች መደረጋቸውን የሚያነሱት ምሁሩ፥ ግን  የተሰጡ አስተያየቶችን እና ምክር ሀሳቦችን ወደ ተግባር የመለወጡ ሂደት አዝጋሚ እና የኤሊ ጉዞ ሆኖ ቆይቷል ነው የሚሉት።

ዶክተር በላይ በግልፅ ውይይት አድርጎ የጋራ መግባባት ላይ መድረስን ይጠይቃል ነው የሚሉት ።

ከፍተኛ ተመራማሪው ግብርናን እንደሌሎች ዘርፎች መመልከት አደጋው የከፋ ነው ይላሉ፤ ዘርፉ  እንደሌላው ቴክኖሎጂ ተሰርቶ የሚወጣ አለመሆኑን በማንሳት።

አቶ ታምሩ ጫልቺሳ  ገለቶ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርና እና እንስሳት ኮሌጅ ውስጥ የገጠር ልማት እና ግብርና ኤክስቴንሽን ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ናቸው።

ለኢትዮጵያ ግብርና የታሰበው ደረጃ ላይ አለመድረስ በዋናነት ሶስት ምከንያቶችን ዘርዝረዋል።

በግብርናው ዘርፍ ላይ በሚደረጉ ምርምሮች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች የኤክስቴንሽን አተገባበር ክፍተት እና የፖሊሲ መናክሎች ተጠቃሾች ናቸው።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የምርምር ኢንስቲቲዩት እና ማዕከላት የሚደረጉ ጥናቶች እና ምርምሮች ተግባር ተኮር መሆን ይጎድላቸዋል ነው የሚሉት።

አብዛኛዎቹ ተመራማሪዎች ቅድሚያ የሚሰጡት ምን ያህል ተነባቢ እና ተፅእኖ ፈጣሪ የምርምር መፅሄቶች ላይ (research journal) ላይ ይታተሙልኛል እንጂ አርሶ አደሩ ላይ ወርዶ ምን ያህል ምርታማነትን ይፈጥራል የሚለው ነጥብ ላይ አይደለም ባይ ናቸው።

አቶ ታምሩ የምርምር ውጤቶች ግምገማ ስርዓትም  ምን ያህል የምርምር መፅሄቶች ላይ አሳትሟል የሚለው አካሄድ መፈተሽ አለበት ይላሉ።

የግብርና ፖሊሲው በራሱ መፈተሽ አለበት የሚሉት ተመራማሪው፥ የኢትዮጵያ የግብርና ፖሊሲ በጥቅሉ ሲታይ መልካም ነው፤ ነገር ግን ለመተግበር መሬት ላይ ሲወርድ የማህበረሰቡን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ እና የተጋነነ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የጅማ ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ሌላኛው ሊፈተሽ ይገባል ያሉት ጉዳይ የኤክስቴሽን ስርዓታችን እና የሚመረቁ የግብርና ባለሙያዎች አቅም ነው።

ተመራቂዎች እንደ የሀገሪቱ የስነ ምህዳር ሁኔታ ያገናዘበ እና ነባራዊ ሁኔታውን የሚረዱ ሆነው መቀረፅ አለባቸው ነው የሚሉት።

ባለሙያዎች ወረቀት እና ፖለቲካ ስራ ላይ መጠመዳቸው ቀርቶ ሙያ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ  መሆን አለበት እንደ አቶ ታምሩ ጫልቺሳ፤ አሁን ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ባለሙያዎች በአድካሚ ግን ፍሬ አልባ በሆኑ ብዙ ስራዎች ላይ የተጠመዱ ናቸው ይላሉ።

ከፍተኛ ተመራማሪው ዶክተር በላይ ባለፉት ዓመታት ተግባር ላይ ዋሉ ስለተባለላቸው የግብርና ቴክኖሎጂ ገሃዳዊ እውነታቸው ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።

አብዛኛዎቹ ቴክኖሎጂዎች የኢትዮጵያን አርሶ አደሮች ነባራዊ እውቅት ከግምት ውስጥ ያስገቡ አይደሉም በማለትም ይከራከራሉ ።

አርሶ አደሩ ድረስ ዘልቀን የምንሰራቸው የምርምር ስራዎች አነስተኛ መሆናቸውን እና የምናወጣቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶችም የአርሶ አደሩን ነባር እውቀት ያገናዘቡ እንዳይደሉ ነው የሚያስረዱት፤ አብዛኛው የምርምር ስራዎች ከምዕራባዊያን እና ከአሜሪካ መፅሃፍት የተቀዱ መሆናቸውን በመናገር።

አርሶ አደሩን እኮ እንዴት በማረሻ እያረሰ እንዳለ እና እንዴት ያን ማረሻ  ማዘመን እንዳለብን ሳናጠና ቀጥታ ወደ ትራክተር ለመሸጋገር እየሞክርን ነው ይላሉ።

አቶ ታምሩ በጥናት የተገኙ  የግብርና ምርምር ውጤቶችን ተግባር ላይ  የማዋሉ አካሄድም መፈተሽ አለበት ባይ ናቸው ።

አዳዲስ የሜካናይዜሽን ውጤቶች እና የምርምር ግኝቶች ለአርሶ አደሮች ተደራሽ እንዳልሆኑ ተናግርዋል።

ቁጥሩ እያደገ ያለው ህዝብን የመመገብ አቅሙ ሲፈተሽ

ዶክተር በላይ አሁን ላይ  ያለው የግብርና አመራረት ሂደት ቀጣይ ከሆነ እየጨመረ ካለው የህዝብ ብዛት አኳያ ራሳችንን የመመገብ አቅማችን ከባድ ፈተና ውስጥ ይወድቃል ነው የሚሉት።

ተመራማሪው ከ30 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል፤ ምን አልባትም 140 ሚሊዮን ይገባል ተብሎ እንደ ተተነበየ ይነገራል።

ይህን ህዝብ ለመመገብ አሁን ከሚመረተው ተጨማሪ 12 ሚሊዮን ቶን ማምረት ይጠይቃል፤ በአሁኑ አስተራረስ ከተሄደ 60 በመቶ ማስፋት ይጠይቃል።

ዶክተር በላይ ይህ የሚያፈናፍን አይደለም፤ ቴክኖሎጂ ላይ ያተከሩ ስራዎች ማምራት ይገባል ባይ ናቸው ።

 መሬት እያላት በበቂ ሁኔታ ማምረት ያልቻለቸው ኢትዮጵያ ከዚህ አዙሪት እንዴት ትውጣ ?

የጅማ ዩኒቨርሲቲው አቶ ታምሩ ምርምር ላይ ትኩረት ይደረግ ባይ ናቸው ። ምርምሮች ግን መደርደርያ የሚያሞቁ እና የጥናት ጆርናሎች ማድመቂያ ሳይሆኑ የአርሶ አደሩን ህይወት የሚቀይሩ ተግባር ተኮር ምርምር መሆን ይገባቸዋል፤ እንደ አቶ ታምሩ ጫልቺሳ ።

አቶ ታምሩ በደላሎች የተሞላውን የግብርና ውጤቶች የገበያ ሰንሰለት ማሳጠር፣ የኤክስቴንሽን ሰርዓቱን ዳግም መፈተሽ፣ የግብርና ፖሊውን ከተነባራዊ ሁኔታው ጋር ማስተሳሰር፣ ለጥናት የሚሰጡ ማበረታቻዎችን ከህብረተሰቡ ተጠቃሚነት አኳያ መመዘን  አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር በላይ ስማኔ በበኩላቸው  የግብርው ዘርፍ የችግሩ መፍቻ ቁልፎች  አራት ናቸው ይላሉ።

የመጀመርያው መግቢያችንም መውጫችንም ገበያ መሆን አለበት፤ ገበያ ሲባል  ስለግብዓት፣  ስለ እህል ሽያጭ፣ ስለ አቅርቦት እና ጥራት መሆኑን ያስረዳሉ።

ሁለተኛ ያደረጉት ደግሞ  የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ሲሆን፥  ሶስተኛው አርሶ አደሩን ከግምት ውስጥ ያስገባ የቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ምርምር፤ በመጨረሻም አሁን ላይ በጥናት ተደረሰበት ያሉት ዶክተር በላይ ለግብርናው ዘርፍ ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚሉትን ዘርዝረዋል።

እንደ ዶክተር በላይ ስማኔ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ማለት ስለ ፖሊሲ ነው፤ ምቹ ሁኔታ ስለ ስነ ምግባር ነው፤ ምቹ ሁኔታ ደንብ እና ስርዓትን በተገቢው ሁኔታ ማስፈፀም ነው እንደ ተመራማሪው ።

 

 

በስላባት ማናዬ

 

 

 

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.