ዛሬ የፈረንጆቹን 2020 አዲስ ዓመት ያልተቀበሉ ሀገራት የትኛዎቹ ናቸው?
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) ዛሬ በዓለም ዙሪያ በርካታ ሀገራት አዲስ ዓመታቸውን 2020 በድምቀት ተቀብለዋል።
ሆኖም ይህንን አዲስ ዓመት ሁሉም የዓለም ሀገር አልተቀበለውም። ማታዶር ኔት የተባለ ድረገፅ 2020 ላይ የማይገኙ ያላቸውን ሰባት ሀገራት ዝርዝር ይዞ ወጥቷል።
ሰሜን ኮሪያ
የጎርጎሳውያኑን የቀን አቆጣጠር የሚከተሉ ሀገራት ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ቀን መሰረት አድርገው አዲስ ዓመታቸው የሚገባበትን ቀን ያሰላሉ። ያንንም አስልተው ዛሬ 2020 ላይ ደርስዋል። ሰሜን ኮሪያውያን ደግሞ በፊናቸው ሀገሪቱ የአምላክን ያህል ክብር የምትሰጣቸው መሪዋ ኪም ኢል ሱንግ የተወለዱበትን ቀን መነሻ በማድረግ የቀን መቁጠሪያቸውን አዘጋጅተዋል። በዚሁ መሰረት ሰሜን ኮሪያውያን 110ኛ ዓመተ ምህረት ላይ ይገኛሉ። ይህ ጁሼ የሚሉት የቀን መቁጠሪያቸው በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር በ1912 ነው የተጀመረው፤ መሪው የተወለዱበት ዓመት።
ታይላንድ
የታይላንድ የቀን አቆጣጠር የቡድሃን እምነት የተመሰረተ ሲሆን፥ በዚህ እምነት የቀን አቆጣጠር መሰረትም ታይላንድ አሁን ላይ 2 ሺህ 563 ዓመት ላይ ትገኛለች።
ከታይላንድ ጋርም ስሪላንካ፣ ካምቦዲያ፣ ላኦስና ማይነማር የቀን አቆጣጠሩን ይከተላሉ።
ኢትዮጵያ
ጥንታዊውን የኮፕቲክ የቀን አቆጣጠርን የምትከተለው ኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠሯ ከጎርጎሳውያኑ የቀን አቆጣጠር በ7 ዓመት ወደኋላ የቀረ ነው። ይህች ጥንታዊት ሀገር አንድ ዓመቷ 13 ወራትን በመያዝ የተለየም ነው ይላል ድረገፁ።
እስራኤል
ጠንታዊቷ እስራኤል ዛሬም የህብራውያንን የቀን አቆጣጠር ትከተላለች። ከጨረቃ መውጣትና መግባት ጋር የተሳሰረው የቀን አቆጣጠሩ ከክርስቶስ ልደት በፊት 7, 3761 የተጀመረ ነው። በዚሁ መሰረት ዛሬ ላይ እስራኤላውያን 5 ሺህ 780ኛ ዓመት ላይ ይገኛሉ።
ኢራን
የኢራናውያን የፋርስ የቀን አቆጣጠር ከኮከብ ቆጠራ ጋር የተሳሰረ ነው። የፋርስ የቀን አቆጣጠር የፀሃይ ሂጅራ የቀን አቆጣጠርም ይባላል። በዚህም መሰረት ኢራን በዚህ እመት 1,398ኛ ዓመቷን ትቀበላለች።
ጃፓን
ንጉሳዊ ስርዓትን እስካሁን ያልጣለቸው ጃፓን የቀን አቆጣጠሯንም በንግስና ላይ ካለው ንጉስ ቆይታ ጋር አስተሳስራለች። አንድ ንጉስ ተነስቶ ወይም ህይወቱ አልፎ በሌላ ሲተካ ዓመትን እንደ አዲስ መቁጠር ይጀምራሉ። ከሁለት ዓመት በፊት አዲስ ንጉስ የተቀባላት ይህች ሀገር 2ኛ ዓመት ላይ ትገኛለች።
ሳዑዲ አረቢያ
ሳዑዲ አረቢያ እንደ አብዛኛዎቹ የአረብ ሀገራት የጎርጎሳውያኑን የቀን አቆጣጠር ከእስላማዊ የቀን አቆጣጠር ጋር ጎን ለጎን ትጠቀማለች። በአስልምና የቀን አቆጣጠር መሰረት ሀገሪቱ 1 ሺህ 442ኛ ዓመት ላይ ትገኛለች።