Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ በህገ ወጥ መንገድ የሚሸጠውን ነዳጅ ለመከላከል መዘጋጀቱን አስታወቀ።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው በክልሉ ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ የተሽከርካሪዎች ቁጥር ከማደጉ ጋር ተያይዞ የነዳጅ ፍላጎተ መጨመሩን ተናግረዋል።

ሆኖም የአቅርቦት እና የፍላጐት አለመጣጣም ችግር በመከሰቱ ችግሩን ለመፍታት የፌደራል መንግስት ከዜጎች ግብር እየሰበሰበና ነዳጅ ላይ ድጎማ እያደረገ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ሲያቀርብ መቆየቱን አንስተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰተ የመጣውን የነዳጅ እጥረት ለመፍታት ወደ ሀገር ውስጥ የገባውን ነዳጅ በአግባቡ በመጠቀም በተቀናጀ እና በተባበረ መልኩ በመስራት በፍትሃዊነት ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ለማድረስ ይሰራል ብለዋል።

ነዳጅን በፍትሃዊነት ለተጠቃሚው ህብረተሰብ እኩል አለማከፋፈል፣ የአቅርቦት መቆራረጥ፣ የጥቁር ገበያ መኖር ለነዳጅ እጥረት መከሰት ምክንያት መሆኑ ይነገራል።

አሁን ላይ በክልሉ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ ማታ ማታ በህገ ወጥ መንገድ የሚሸጠውን ነዳጅ ለመከላከል ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ንጋቱ አንድ ሰዓት ነዳጅ እንዳይሸጥ ለመከልከል ታቅዷል ነው የተባለው።

መረጃው የአማራ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ነው፤

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.