Fana: At a Speed of Life!

እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ ንቅናቄ በሀረሪ እና አፋር ክልል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሎቹ ጤና ቢሮዎቹ ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 4 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ ንቅናቄ በሀረሪ እና አፋር ክልል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሎቹ ጤና ቢሮዎቹ ገለጹ።
የሁለቱ ክልሎች ጤና ቢሮዎች ለፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ማህበረሰቡ ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ የሚሆንባቸው አካባቢዎችን በመለየት ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው ።
ቫይረሱን ለመከላከል ያስችላል የተባለው ንቅናቄ በክልሎቹ እስከ ቀበሌ ድረስ እየተሰራበት ሲሆን የተጠያቂነት አሰራርም ተዘርግቶለታልም ነው ያሉት።
ቫይረሱ እያደረሰው ያለውን ማህበራዊ ቀውስ ለመቀነስ በሀገር አቀፍ ደረጃ የማስክ ያድርጉ ንቅናቄ ተጀምሯል።
የሀረሪ ክልልም ይህንን ንቅናቄ መሰረት በማድረግ ከፍተኛ የጥንቃቄ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ነው የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብሳ ኢብራሂም ለጣቢያችን ተናግረዋል።
በንቅናቄ ዘመቻው ለ 6 ወር የሚቆይ እቅድ በማውጣት በካቢኔ ደረጃ በተዋቀረ ኮሚቴ መጀመሩን ገልጸዋል።
የንግድ ኮሪደር በሆነችው ሀረሪ ክልል የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት የጤና ቢሮ ሀላፊው ÷ በክልሉ ከ 2 ሺህ 800 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 60 ያህሉ ደግሞ ለሞት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ ያለው ተጋላጭነትም 7 ነጥብ 4 በመቶ ላይ ደርሷል።
ተጋላጭነቱም ሆነ የሞት ምጣኔው በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለው በላይ የሆነባት ሀረሪ አሁን በተጀመረው ንቅናቄ ውጤታማ ስራን ለመስራት መታቀዱን ተናግረዋል።
የአፋር ክልልም በቫይረሱ ከ 1ሺህ 800 ባለይ ሰዎች የተያዙበት እና 6 ሰዎች የሞቱበት በማስክ ያድርጉ ንቅናቄ ለውጥን ለማምጣት እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ያሲን ሀቢብ÷ ንቅናቄው ከተጀመረ በኋላ የተወሰኑ ለውጦች እየታዩ ነው ብለዋል።
አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ አገልግሎቱን ለማግኘት ማስክ ማድረግ ቢኖርም አገልግሎቱን ካገኙ በኋላ ማስኩን ያለማድረግ ችግሮችም በክልሉ መታየታቸውን አብራርተዋል።
በተለይም ህብረተሰቡ በስፋት በሚገኝባቸው እና በሚገለገልባቸው ቦታዎች ሰፊና ጥብቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን የነገሩን አቶ ያሲን÷ በክልሉ ርእሰ መስተዳድር የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮም ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
ከ 5 መቶ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችም በዚህ ስራ ላይ መሰማራታቸውን አብራርተዋል።
እንደ ስራ ሀላፊዎቹ ከሆነ በሁለቱም ክልልች በንቅናቄው እስከ ቀበሌ ድረስ ሰፊ ሰራዎችን ለመከወን ነው እንቅስቃሴ እየተደረገ ያለው።
በተለይም በትራንስፖርት ፣በሀይማኖት እና መሰል ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ትኩረት የሚደረግ ሲሆን የፀጥታ አካላትም የሚሳተፉበት ነው።
ይህ ሲደረግ ግን ተጠያቂነት የሚያስከትሉ አሰራሮችም መዘርጋታቸውን አቶ ኢብሳ እና አቶ ያሲን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ የግንዛቤ ችግር ባይኖርበትም ገንዛቤውን ወደ ተግባረ መቀየር ላይ ያለው ክፍተት አሁን ላለው ስርጭት መጨመር ምክንያት ነው ብለዋል።
አሁን ያለንበት ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአላት እና የሰርግ ስነ ስርአቶች በስፋት የሚከወኑበት መሆኑን መነሻ በማድረግም በልዩ ሁኔታ ቁጥጥር ለማድረግም እየተሰራ መሆኑን ሀላፊዎቹ ተናግረዋል።
ለዚህ ውጤታማነት የንቅናቄ ተግባሩን በርካታ አካላትንም በማሳተፍ ነው እየተሰራ ያለው ነው ያሉት።
በሚሰራው ንቅናቄ የቫይረሱን ስርጭት እንዲገታ ለማድረግ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም የስራ ሀላፊዎቹ መልእክት አስተላልፈዋል።
በዙፋን ካሳሁን
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.