Fana: At a Speed of Life!

የሃይማኖት መሪዎች ለክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 27 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን ከክፋት እና ጥፋት መንገድ በመራቅ የሀገራቸውን ሰላም እንዲጠብቁ የሃይማኖት መሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።
የሃይማኖት መሪዎቹ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፥ ሰላም ሲደፈርስ የህብረተሰቡ ኑሮ ይናጋል፤ ድህነት እና ችግርም ይንሰራፋል ነው ያሉት።

እናም የሁሉም ነገር ህልውና የሆነውን ሰላም መጠበቅ የህብረተሰቡም የመንግስትም ሀላፊነት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው፥ ከክፉ ስራ ራስን በመጠበቅ መልካም ነገሮችን ለመፈፀም መትጋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በጠላትነት ከመተያየት ይልቅ እርስ በርስ በመፋቀር እና በመተሳሰብ የቆየ የመኖር ልምዱን እንዲያስቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃድቁ አብዶ በመልካም ምኞት መልዕክታቸው። ከአመፅ በመራቅ ሰላምን ማስፈን ላይ ሁሉም የጋራ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሰላምን ተግተው የሚሰብኩ እና ለአብሮነት እሴት መጎልበት የሚደክሙ የመልካም ልብ ባለቤቶች እንዳሏት ያነሱት ፓስተር ፃድቁ፥ እኛም የእነሱን አርአያነት ልንከተል ይገባል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

የሃይማኖት መሪዎቹ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው ክርስቲያኖች የገና በዓልን ሲያከብሩ አቅመ ደካሞችን መርዳት፣ የታመሙትን መጠየቅ እና የታሰሩትን መጎብኘት ሊዘነጉት እንደማይገባም አሳስበዋል።

የክርስቶስ ልደት በዓልን በሌሎች መልካም ተግባራት ማሳለፍ እንደሚገባም አንስተዋል።

በፋሲካው ታደሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.