ቦርዱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን አስመልክቶ መመሪያ አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ 1162/2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን አስመልክቶ መመሪያ ማፅደቁን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ታህሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በቦርዱ ተመዝግበው የሚገኙ የአገር አቀፍና የክልል ፓርቲዎች (በአዋጅ ቁ. 1162/2011 መሰረት) ማሟላት ያሉባቸው ግዴታዎች መመርያ አፅድቋል።
መመሪያው ከመጽደቁ በፊት ከፓርቲዎች ጋር የተለያዩ ውይይቶች መደረጋቸውን የጠቆመው ቦርዱ፥ ሰባት ፓርቲዎች በጽሁፍ ግብአታቸውን ማስገባታቸውን ነው ያመለከተው።
በፀደቀው መመሪያ የተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ዝርዝሯል። በዚሁም መሰረት፦
1.ሁሉም ተመዝግበው የሚገኙ የፓለቲካ ፓርቲዎች በአዋጅ 1162/2011 የተቀመጠውን የመስራች አባላት ፊርማ ለማሟሟላት ሁለት ወራት የጊዜ ገደብ አላቸው፡፡
2.ጠቅላላ ጉባኤ ሳያካሂዱ ጊዜ ያለፈባቸው ፓርቲዎች በአዋጅ 1162 መሰረት አሟልተው በሁለት ወር ውስጥ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
3.ጠቅላላ ጉባኤ በወቅቱ ያካሄዱ አገር አቀፍ ፓርቲዎች በአዲሱ አዋጅ 1162 ላይ የተቀመጠውን የጠቅላላ ጉባኤ መስፈርት በሟሟላት እስከ ጥር 2013 ዓ.ም ድረስ አጠናቀው ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡
4.ጠቅላላ ጉባኤ በወቅቱ ያካሄዱ ክልላዊ ፓርቲዎች በአዲሱ አዋጅ 1162 የተቀመጠውን የጠቅላላ ጉባኤ መስፈርት ለሟሟላት እስከ ታህሳስ 2013 ድረስ አጠናቀው ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡
5.በቦርዱ ያልተመዘገቡ ነገር ግን በቀድሞው ህግ በሂደት ላይ ያሉ፣ በቀድሞ መሟላት ያለበትን አጠናቀው በአዲሱ አዋጅ ያሉትን መስፈርቶችም ጨምረው በጋራ ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
6.አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎችን ህጉ ላይ ያለውን የመስራች አባላት ቁጥር ከሟሟላት መስፈርት ነጻ ናቸው ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሁሉም የተመዘገቡ እና በሂደት ላይ ያሉ የፓለቲካ ፓርቲዎች ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርትና እና ጊዜ ገደብ የሚገልጽ ደብዳቤ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ለሁሉም ፓርቲዎች እንደሚያደርስ ገልጿል።