Fana: At a Speed of Life!

በ6 ወራት በትራፊክ አደጋ የ1 ሺህ 848 ሰዎች ህይወት አልፏል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት  በሀገር ዓቀፍ ደረጃ 20 ሺህ 672 የመንገድ ትራፊክ አደጋ መድረሱን እና የ1 ሺህ 848 ሰዎች ህይወት ማለፉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የትራፊክ አደጋዎቹ ከሐምሌ 1 ቀን 2012 እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ባለው 6 ወራት ጊዜ ውስጥ የደረሱ መሆናቸውን በኮሚሽኑ የወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት የወንጀልና ትራፊክ መረጃ ትንበያ ገልጿል።

ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት የወንጀል ትራፊክ መረጃ ትንበያ ተወካይ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር መስፍን አይተነው በ2 ሺህ 646 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው፥ 2 ሺህ 565 የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ለቀላል የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም 495 ሚሊየን 240 ሺህ 473 የሚገመት ንብረት መውደሙንም ገልፀዋል፡፡

በትግራይ ክልል ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የትራፊክ አደጋ መረጃ እንዳልደረሳቸው የገለጹት ኢንስፔክተር መስፍን መረጃው ከትግራይ ክልል ውጭ ከሁሉም ክልሎች የተሰበሰበ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተመዘገበው የትራፊክ አደጋ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 15 ሺህ 844 የትራፊክ አደጋ መድረሱን፣192 ሰዎች በአደጋው ምክንያት ህይወታቸውን ማጣታቸውን እንዲሁም በ846 ሰዎች ላይ ከባድ፣ በ512 ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው መናገራቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የመንገድ ትራፊክ አደጋውም በአሽከርካሪዎች ስነ-ምግባር ጉድለት፣ ቸልተኝነት እና ብቃት ማነስ፣ በተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ጉድለት፣ ወቅቱን የጠበቀ የቦሎ እድሳት ባለማድረግ፣ በመንገድ ግንባታ ችግርና በእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ችግር እንደሚከሰትም ጠቁመዋል፡፡

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.