Fana: At a Speed of Life!

ጠላቶቻችን የጸረ-ድህነት ጉዟችንን ለማደናቀፍ ቀን ከለሊት እየሰሩ ይገኛሉ-ወ/ሮ አዳነች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) -“ድምፃችን ለነፃነታችን እና ለሉአላዊነታችን” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ስቴድየም ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ።
ሰልፉ የውጭ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነትና ተፅእኖ ለማውገዝ ፣ እንዲሁም ወጣቶች ለሀገራቸው ድምፃቸውን ለማሰማት ያለመ ነው።
በሰልፉ ላይ “ኢትዮጵያ ሞግዚት አትፈልግም!፣የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የያዘውን የተሳሳተ አቋም በድጋሜ እንዲያጤነው እንጠይቃለን!፣ግድቡ የኔ ነው!” የሚሉ መልዕክቶች በወጣቶቹ ተላልፈዋል፡፡
በተጨማሪም “በሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ሉአላዊነትን መዳፈር ነው!፣ ኢትዮጵያውያን ለውጭ ጫና አንበረከክም!፣ መሪዎቻችንን ራሳችን እንመርጣለን!” የሚሉ መፈክሮች ተሰምተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ጥቅማቸውና በውጭ ኃይሎች ጥቃት አንድም ጊዜ ተለያይተው አያውቁም ብለዋል፡፡
ወጣቶች የውጪ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነትና የውስጥ ባንዳዎችን ሴራ ለማውገዝና ለመላው የዓለም መልዕክት ለማስተላለፍ ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ማንንም ለመጉዳትና ለመበደል እንደማይሹ ሁሉ ማንም እንዲጎዷቸውና እንዲበድላቸው እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።
ጠላቶቻችን ከድህነት የመውጣት ጉዟችንን ለማደናቀፍ ከተቻላቸውም ለማስቆምና ህዝባችንን ለልመናና ለረሃብ ለመዳረግ ቀን ከለሊት እየሰሩ ይገኛሉ ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በራሳችን ገንዘብና ጉልበት የምንገነባው የታለቁ የህዳሴ ግድባችን ሁለተኛ ዙር ሙሌት ለማደኛቀፍ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም ያሉት ምክትል ከንቲባዋ አባይን በፍትሃዊነት የመጠቀም መብታችንን ከማረጋገጥ ወደ ኋላ አንልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
“የኛ የውስጥ ጉዳይ የኛ ብቻ እንጂ፣ የማንንም ጣልቃ ገብነት የማይሻ በመሆኑ ከዚህም የዘለለ ጣልቃ ገብነት ሉዓላዊነትን መድፈር መሆኑ ጭምር ሊታወቅ ይገባል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሰልፉ ላይ በርካታ ወጣቶች ተሳትፈዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.