Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ዓለም አቀፍ ጫና ሉዓላዊነትን የሚጋፋ ነው – የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ዓለም አቀፍ ጫና አግባብነት የሌለውና የሀገሪቷን ሉዓላዊነት የሚጋፋ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዛሬ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት በማድረግ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች ለመሻገር ውስጣዊ ሰላሟን መጠበቅ፣ የጋራ መግባባትና አንድነት መፍጠርና የውጭ ግንኙነትን ማጠናከር ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አንስቷል።

የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ችግሮች በዘላቂነት የሚፈታ በመሆኑ ካርድ የወሰዱ ዜጎች በሙሉ በዕለቱ ድምፅ እንዲሰጡም ጠይቋል።

አንዳንድ የውጭ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አረዳድ ትክክል እንዳልሆነ የጠቀሰው መግለጫው ÷ በተለይም በቅርቡ በአሜሪካ መንግሥት የተጣለው የቪዛ እገዳ ትክክል አለመሆኑን ገልጿል።

እየደረሰ ያለውን የውጭ ጫና ለመቋቋም የጋራ ምክር ቤቱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን በመተው በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል።

የውጭ ግንኙነቱ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት በቀጣይ በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም ነው ያመለከተው።

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ በምታደርገው የሰላም ማስከበርና ተያያዥ ሥራዎች ትልቅ ተግባር እያከናወነችና ተሰሚነት ያላት ሀገር መሆኗም ተነስቷል።

በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የሚመጡ ጫናዎች የሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን ነው የምክር ቤቱ መግለጫ ያመላከተው፡፡

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን በመገንዘብ ግድቡ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ሁሉ በማድረግ ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ መቅረቡን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.