Fana: At a Speed of Life!

የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ግንባታ ከስጋት ወጥቶ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በግንባታ መዘግየትና የጥራት ችግር ምክንያት ስጋት ውስጥ የነበረው የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የቦርድ አባላት፣ የስራ ኃላፊዎች እና ጋዜጠኞች ዛሬ የፕሮጀክቱን አፈፃፀም በስፍራው በመገኘት ጎብኝተዋል።

ግንባታው 2003 ዓ.ም በቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ቢጀመርም መሃል ላይ በተስተዋሉ የግንባታ ጥራት እና መዘግየት ችግር ምክንያት 2010 ዓ.ም እንዲቋረጥ ተደርጓል።

በድጋሚም 2011 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ግንባታውን ሌላ ተቋራጭ እንዲጨርሰው መሰጠቱ ነው የተገለፀው።

ግንባታውን ለማከናወን የተረከበው የቻይናው ካምሲ (ሲ ኤ ኤም ሲ) ኩባንያ ባለፈው መስከረም ወር ላይ ስምምነት በመግባት ግንባታውን ጀምሯል።

ኩባንያው ቀደም ሲል በተከናወነ የግንባታ ስራ የጥራት መጓደል ያለባቸውን ክፍሎች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል በማፍረስ ግንባታውን እያከነወነ እንደሚገኝም ተመልክቷል።

አሁን ላይ ግንባታው 67 በመቶ የተጠናቀቀ መሆኑን እና በሚቀጥለው ግንቦት ወር ላይ ወደ ሙከራ ምርት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወዮ ሮባ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

የጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት በሀገሪቱ ካሉ መሰል የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች በተለየ ምቹ ከባቢ ላይ የሚገኝ ሆኖ ሳለ በሀብቱ ሳንጠቀም ቆይተናልም ነው ያሉት።

ጉድለት የነበረባቸውን የግንባታ ፕሮጀክቱን ስራዎች አስተካክሎ ከስጋት በማስወጣት እና ተጨማሪ ስራዎችን በማከናወን በታህሳስ ወር 2013 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የፋብሪካው ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ይጠናቀቃል በሚል 2004 ላይ የአገዳ ተከላ መከናወኑን ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው፥ ግንባታው በዚህ መልኩ በመዘግየቱ አሁን ላይ 13 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ አገልግሎት የማይሰጥ አገዳን መቁረጥ ይገባል ብለዋል።

አንድ የሸንኮራ አገዳ ምርታማ እንዲሆን ተተክሎ ከ14 እስከ 16 ወራት ባለው እድሜው ውስጥ መቆረጥ የሚገባው ሲሆን፥ አሁን ላይ ያለው አገዳ 60 ወራት የሞላው በመሆኑ ለአገልግሎት መዋል አይችልም ተብሏል።

በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ ከመንግስት 215 ሚሊየን ብር በማስፈቀድ ቆረጣውን ለማከናወን ገንዘብ እስከሚለቀቅለት ድረስ እየተጠባበቀ መሆኑንም ነው ዋና ስራ አስፈፃሚው ያመለከቱት።

በዚህ ፕሮጀክት እያንዳንዳቸው በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያላቸው ሁለት ስኳር ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ግንባታቸው ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም በከፍተኛ የግንባታ መጓተት ምክንያት በስኳር ኮርፖሬሽንና በሜቴክ መካከል በ2004 ዓ.ም.ተደርሶ የነበረው የጣና በለስ ቁጥር 1 እና 2 ስኳር ፋብሪካዎች የግንባታ ውል እንደ ቅደም ተከተላቸው በ2010 ዓ.ም. እና 2009 ዓ.ም. በመንግሥት ውሳኔ እንዲቋረጥ ተደርጓል።

የፋብሪካዎቹ ቀሪ የግንባታ ሥራዎች ተጠናቀው ወደ ምርት ሲገቡ በ40 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማን የሸንኮራ አገዳ በግብዓትነት ይጠቀማሉ።

ለሸንኮራ አገዳ ልማት የሚውለው የመስኖ ውሃ የሚገኘው በበለስ ወንዝ ላይ በተገነባ የውሃ መቀልበሻ ዊር አማካይነት ነው።

ፋብሪካዎቹ ሙሉ የማምረት አቅማቸው ላይ ሲደርሱ እያንዳንዳቸው በዓመት 2 ሚሊየን 420 ሺህ ኩንታል ስኳር እና 20 ሚሊየን 827 ሺህ ሊትር ኢታኖል የማምረት አቅም ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ የሚገኝ ነው።

በፍሬህይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.