Fana: At a Speed of Life!

የጌዲኦ ብሔር የዘመን መለወጫ (ዳራሮ) በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጌዲኦ ብሔር የዘመን መለወጫ (ዳራሮ) በዓል በዲላ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳውን ጨምሮ የተለያዩ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የብሔሩ አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ታድመዋል።

በዓሉ በዲላ ከተማ ስታዲየም በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች እና ስነ-ስርዓቶች ነው እየተከበረ የሚገኘው።

በስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፥ በክልሉ የሚገኙ ባህላዊ እሴቶችን በተገቢው ሁኔታ በመጠበቅ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በብሔር እና በሃይማኖቶች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው፥በቅርቡ በአካባቢው ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ  እንዲመለስ ድጋፍ  ላድረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በመወያየት እና በመነጋገር መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ጠቃሚ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ እሴቶችን ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍም የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.