Fana: At a Speed of Life!

ወጪ እንድትቀንስ የተነገራት ጃፓናዊት ሞዴል ትዳሯን በሳምንቱ አፍርሳለች

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ካቶ ሳሪ የተባለችው ጃፓናዊት የ29 ዓመት ሞዴል ወጪዋ በመብዛቱ በተጋባች በሳምንቷ ትዳሯን አፍርሳለች።

ሞዴሏ ቅንጡ በሆነው የህይወት ዘይቤዋ እና ውድ ዋጋ ላላቸው የፋሽን አልባሳት ከፍ ያለ ፍቅር እንዳላት ይነገራል።

ስሙ ያልተጠቀሰውና በቤት ግንባታ ዘርፍ የተሰማራው ግለሰብ ከሞዴሏ ጋር በግንቦት ወር 2019 ነበር ግንኙነት የጀመረው።

ከተገናኙ በኋላ ከጋብቻ በፊት በሶስት ወር ከ15 ቀናት ውስጥ ሞዴሏ 9 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ወጪ ማድረጓ ተነግሯል።

ይህም ሆኖ ባለሀብቱ ከሞዴሏ ጋር ትዳሩ እንዲቀጥል ፍላጎት ነበረው።

የገንዘቡ መብዛት ያሳሰበው ባልም ጋብቻ ከፈጸሙ በኋላ ወጪዋን እንድትቀንስ ቢነግራትም ሚስት ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለችም።

የባሏን ሃሳብ ውድቅ ያደረገችው ሚስትም ትዳራቸው እንዲፈርስ ጥያቄ አቅርባለች።

ሞዴሏ ትዳራቸው እንዲፈርስ በተጋቡ ሳምንት ውስጥ ጥያቄዋን ማቅረቧን በዩቲዩብ ቻናሏ ላይ የገለፀች ሲሆን በወቅቱ ባለቤቷ ወጪሽን ቀንሺ ሲላት መቆጣቷን ገልፃለች።

ባለቤቴ አሳስቶኛል የምትለው ግለሰቧ ከመጋባታቸው በፊት ስታወጣ እንደነበረው ከትዳር በኋላም እንደፈለኩት ወጪ እንዳወጣ ይፈቅድልኛል ብየ አስቤ ነበር ብላለች።

ካቶ ሳሪ በሳምንት ውስጥ ትዳሯን በማፍረሷ ከአድናቂዎቿ ቁጣ አስተናግዳለች፤ ለገንዘብ ስትል ነው ያገባችው በማለት የወቀሷትም አልጠፉም።

ሞዴሏ በበኩሏ ሴቶች አርግዘው ልጅ ይወልዳሉ፤ ወንዶች ደግሞ ሰርተው በቂ ገንዘብ ለቤተሰቦቻቸው ያቀርባሉ ስትል የቀረበባትን ወቀሳ አጥጥላለች።

ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.