ሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከኬኒያው ኪሱሙ ብሄራዊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በጋራ ለመስራት ተፈራረመ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)ሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከኬኒያው ኪሱሙ ብሄራዊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በትብብር ለመስራት የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡
የትብብር ስምምነቱ ለሁለቱ ኮሌጆች ተማሪዎችና መምህራን ለልምድ ልውውጥና ዕውቀት ሽግግር ከሚያበረክተው አስተዋፅዖ ባሻገር የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከርም ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል፡፡
የኬኒያ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ሀሰን ኑር ሀሰን እንደገለጹት÷ የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈረሙ በሁለቱ ሀገራት ተማሪዎችና መምህራን የልምድ ልውውጥና የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡
በኬኒያም ሆነ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪው የሚፈልገው አንድ አይነት ባለሙያ በመሆኑ ብቁና ተቀራራቢ ዕውቀት ያላቸው ሙያተኞችን ለማፍራት በእጅጉ ያግዛል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያና ኬኒያ በተለያዩ ጉዳዮች ብዙ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን መፈራረማቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ÷ ይህ ስምምነትም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ከሚያጠናክሩ ጉዳዮች መካከል የሚካተት ነው ብለዋል፡፡
በኬኒያ ኪሱሙ ብሔራዊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዳይሬክተር ካትሪን ኬላኒያ በበኩላቸው÷ ሌሎች ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎችም በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የትምህርት ዘርፎችም በትብብር ለመስራት ስምምነቶች ቢያደርጉ መልካም ነው ብለዋል፡፡
በሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኢስትሪፕ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አለባቸው ኃይሉ እንደተናገሩት÷ የጋራ መግባቢያ ሰነዱ መፈረሙ ተማሪዎችና መምህራን በልምድ ልውውጥ ከሚያገኙት ክህሎት ባለፈ ትስስሩን በማጠንከር እኩል ተቀባይነት ያለው ሥልጠና ለመስጠትና አንዱ ሀገር የተመረቀ ተማሪ ሌላኛው ሀገር ሄዶ የሥራ ዕድል እንዲያገኝ ያስችላል፡፡
በታምራት ቢሻው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!