Fana: At a Speed of Life!

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሰማሩ ባለሃብቶች በዓለም ገበያ የመወዳደር አቅም ያላቸው መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ባሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሰማሩ ባለሃብቶች በዓለም ገበያ ላይ የመወዳደር አቅም ያላቸው መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
ለኢንዱስትሪ ምርቶች ለአፍሪካ አገራት ከተሰጠው ከቀረጥና ኮታ ነፃ የሆነ የገበያ እድል በተጨማሪ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገራችን የሚመጡት በተመጣጣኝ የሠራተኛ ክፍያ፣ ዘመናዊ የፓርኮች መሰረተ ልማቶችና የተሟላ አገልግሎት በአንድ ማዕከል ስለሚያገኙ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ገልጸዋል፡፡
የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን የማሻሻልና የመደረሻ ገበያዎችን የማስፋት ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው÷ በግንባታ ዕቃዎች፣ በፋርማሲዩቲካል፣ የብቅልና ኬሚካልን ጨምሮ ከ100 በላይ የውጭ ኩባንያዎች በፓርኮቹ እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል።
በ13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከተገነቡት ከ270 በላይ ሼዶች መካከል 89 በመቶ የሚሆኑት በባለሃብቶች ተይዘው እየለሙ መሆኑንና 60 በመቶ የሚሆኑት ወደ ስራ መግባታቸውንም ተናግረዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ 750 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱን አስረድተዋል።
በዘርፉ ከ85 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል ያሉት ስራ አስፈጻሚው÷ በተለይ የመብራት፣ የውሃና የኮንቴይነር ችግሮችን ለመቅረፍ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በፓርኮቹ ገብተው የወጭና የገቢ እቃዎችን እንዲያመርቱ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሳንዶካን ደበበ አመልክተዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.