Fana: At a Speed of Life!

በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦች ጥፋተኛ ተባሉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው ግለሰቦች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈ፡፡

ግለሰቦቹ ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አምስተኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ጥቅምት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ነው ውሳኔውን ያስተላለፈው፡፡

ወንጀሉ የተፈፀመው ከሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ የቀድሞ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር፥ ለክልሉ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መማሪያ የሚሆን 578 ሺህ 274 መጽሐፍቶች በ18 ሚሊየን 990 ሺህ ብር ታትሞ እንዲቀርብ የግዢ ውል በማያያዝ መሆኑን የፍርድ ቤቱን ምርመራ ጠቅሶ ሪፖርተር ዘግቧል።

ግዢውን ከመንግሥት የግዢና አስተዳደር መመሪያ ውጪ በተያያዘ ውል ስምምነት ለመፈጸም የቀድሞ የኒያላ ኢንሹራንስ ጂጂጋ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ይሠሩ የነበረው አቶ አብዲ የሱፍ የኢንሹራንሱን የዋስትና ስምምነት መመሪያና አሠራር ጥሰዋል ነው የተባለው፡፡

በዚህም ከኃላፊነታቸው ውጪ የቅድሚያ ማስያዣ ሳያስይዙ ያለ አግባብ ለአቶ ቴድሮስ አዲሱ 15 ሚሊየን 306 ሺህ 803 ብር ክፍያ እንዲከፈል ማድረጋቸውን ዐቃቤ ሕግ በምስክሮችና በሰነድ ማስረጃዎች ማረጋገጥ መቻሉ በውሳኔው ተመላክቷል።

የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው አቶ አብዲ የሱፍ መሐመድና የሶማሌ ፕሪንቲንግ ፕሬስ ድርጅት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) ክፍያው ተከፍሏቸው የተማሪዎቹ መጽሐፍቶች አሳትመው ማቅረብ ሲገባቸው ያላቀረቡ በመሆናቸው የሙስና ወንጀል አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13(1ሐ እና 3) መተላለፋቸው በመረጋገጡ፣ በቀረበባቸው የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ጥፋተኛ መባላቸውን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

የተከሳሾቹን መከላከያ ማስረጃዎችን የመረመረው ፍርድ ቤቱ በተሳትፎ ደረጃቸው በተከሰሱበት አንቀጽ ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በማስረጃ በመረጋገጡ የጥፋተኝነት ፍርድ እንዳስተላለፈ ጠቁሞ ÷ የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ለመጠባበቅ ለጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙን ከስነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.