Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በየሣምንቱ እሁድ የንግድ ባዛር ይዘጋጃል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ እንዲሁም በምርት አቅርቦትና ስርጭት የሚፈጠረውን ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት ለመቀነስ እንዲያስችል ታስቦ ባዛር ማዘጋጀት ማስፈለጉን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባዛሩ በዋናነት በአቅራቢውና በሸማቹ መካከል የሚገኘውን የአቅርቦት ሰንሰለት ለማሳጠርና የገበያ አማራጮችን ለማስፋት አላማው ያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ገልጸዋል።
ለንግድ ባዛሩ የመጀመሪያ ዙር 20 ቦታዎች መዘጋጀታቸውን የጠቆሙት ኃላፊው÷ የፊታችን እሁድም የትራንስፖርት መዳረሻ እና የሕዝብ ብዛትን መሠረት በማድረግ÷ በመገናኛ፣ ፒያሳ፣ ሜክሲኮ አደባባይ፣ ቃሊቲ መናኸሪያ እና ጀሞ 67 ቁጥር ማዞሪያ የሙከራ ስራ ይጀመራል ብለዋል።
በባዛሩም ከግብርና ምርቶች÷ የጤፍና የስንዴ ዱቄት፣ የባልትና ውጤቶች፣ ጥራጥሬና እህሎች እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬዎች ይቀርባሉ፡፡
ከኢንዱስትሪ ምርቶች ደግሞ÷ ዘይት፣ ማካሮኒና ፓስታ ይቀርባሉ ብለዋል ኃላፊው፡፡
የዚህ ባዛር ዓላማም በዋናነት ትኩስ የግብርና ምርቶችን ለሸማቹ ማድረስ፣ በአምራችና በሸማቹ መካከል ያለውን የአቅርቦት ትስስር በማሳጠር አማራጭ የግብይት ስፍራን መፍጠር እንዲሁም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ጫና መቀነስ መሆኑን አቶ አደም ተናግረዋል፡፡
በባዛሩ አቅርቦት ላይም÷ በኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኅብረት ስራ ማህበራትና አርሶ አደሮች፣ የአዲስ አበባ ኅብረት ስራ ማኅበራት፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የሰብልና አትክልት አቅራቢዎች ወይም የጅምላ ነጋዴዎች እና በምግብ ማቀነባበር የተሰማሩ ፋብሪካዎች እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡
በሃይማኖት ኢያሱ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.