Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፍ የመምህራን ቀን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ

•መምህራን ለሀገር ዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መምህራን ለሀገር ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ ለኢዜአ እንደገለጹት ለሰላም መረጋገጥ ትምህርት ትልቁ መሣሪያ ነው።

ሰላም ሲደፈርስ በትውልድ አዕምሮ ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ ከፍተኛ በመሆኑ በሁሉም እርከን ትምህርት ቤቶች የሚገኙ መምህራን ስለሰላም እንዲያስተምሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ምክንያት ከ7 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን የጠቆሙት ዶክተር ዮሐንስ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል።

ጦርነት በሌለባቸው አከባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም የተፈናቃይ ዜጎች መቆያ በመሆናቸው የትምህርቱን ዘርፍ በእጅጉ መጉዳቱን አመልክተዋል።

የሙያ ማህበሩ የተፈናቀሉ ተማሪዎችንና መምህራንን መልሶ ለማቋቋምና ተፈናቃይ ተማሪዎች ባሉበት ሆነው ትምህርት እንዲያገኙ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚሁ ተግባር ሁሉም አካል የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህርትና በሰላም ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶክተር ድሪቧ ደበበ በበኩላቸው፥ ትምህርት ያለሰላም ሊሳካ እንደማይቻል አመልክተዋል።

ትምህርት የትውልድን ዕውቀት፣ አመለካከትና ክህሎትን በማዳበር ለሰላም ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ተናግረዋል።

ትምህርት የሰው ልጅን ክፉ አድርጎ አይቀርጽም” ያሉት ዶክተር ድሪቧ፤ ”በአገራችን ሰላማችን እየተመሰቃቀለ ያለው እኛ መምህራን የሚጠበቅብንን ሃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታችን ምክንያት ነው” ብለዋል፡፡

የማህበረሰቡ እውቀት ፣ ልማድና አስተሳሰብ እንዲሁም የሃይማት ተቋማትና የባህል መሪዎች ሰላምን በማስፈን ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ ምቹ ሁኔታ መኖር እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ህዝብና አገር ተለያይቶ የሚታይ አለመሆኑንና የኢትዮጵያ አንድነት በቀላሉ የሚፈርስ አለመሆኑን ትውሉዱ እንዲረዳ በማድረግ እንዲሁም ለሀገር ዘላቂ ሰላም አዲሱ የትምህርት ፊኖተ ካርታ ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ያስረዱት ደግሞ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አበበ ናቸው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ28ኛ ጊዜ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ በተከበረው ዓለም አቀፍ የመምህራን ቀን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸው 16 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በበአል ስነ ስርአቱ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ የሙያ ማህበሩ ስራ አስፈጻሚ አካላት ተሳትፈዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.